የኢትዮጵያ ፍላጎት አስተማማኝ የባሕር በር በሠላማዊ መንገድ ማግኘት ነው

 – የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ምክክር በስምምነት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፍላጎት ደኅንነቱ የተረጋገጠ እና አስተማማኝ የባሕር በር ሠላማዊ በሆነ እና ሁሉንም ጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ማግኘት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ በአንካራ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮ-ሶማሊያ ውይይት በመሪዎች ደረጃ በተደረገ ምክክር ሁለቱንም ሀገራት በሚያግባባ መልኩ በአሸናፊነት ተቋጭቷል። ይህን ተከትሎም ሁለቱ መሪዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በኩል ዘላቂና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት አማራጭ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ፍላጎት ደኅንነቱ የተረጋገጠ እና አስተማማኝ የባሕር በር ሠላማዊ በሆነ እና ሁሉንም ጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ማግኘት መሆኑን ደግሜ ማረጋገጥ እወዳለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ እያደገ ያለው ወጣት የሚበዛበት የሕዝብ ቁጥራችን እና እየጨመረ ያለው ኢኮኖሚያዊ መሻታችን ይህን ወቅታዊ እና አስፈላጊ አድርጎታል” ነው ያሉት።

እየጨመረ ላለው ለዚህ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና መሻት ምቹ ሁኔታን መፍጠር በቀጣናው ደረጃ ሊፈጥረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንደ መከላከል ሊወሰድና ከጥርጣሬ ይልቅም በትብብር መንፈስ ሊፈፀም እንደሚገባው ተናግረዋል።

“ገንቢ ውይይታችንም አዲሱን ዓመት በትብብር መንፈስ፣ በወዳጅነት እና አብሮ በመሥራት ፍላጎት እንድንቀበለው የሚያስችለን ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጎረቤት ሀገራት እንደመሆናቸው ለምዕተ ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሁለቱ ሕዝቦች ጎረቤታሞች ብቻ ሳይሆኑ ዕጣ ፈንታቸው በደም የተሳሰረ ወንድማማች እና እህትማማች ሕዝቦች መሆናቸውን አውስተዋል።

ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን የጋራ የዘር ግንድ፣ ቋንቋ እና ባሕል የሚጋሩ ብቻ ሳይሆኑ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የሶማሊያ ሀገረ መንግሥትን ደኅንነት ከአሸባሪ ኃይሎች ለመጠበቅ በከፈሉት የደም መስዋዕትነት ጭምር የተሳሰሩ ናቸው ብለዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት በሁለቱ መንግሥታት መካከል ውይይት ለማመቻቸት ጥረት ያደረጉ አካላትን በእጅጉ እንደሚያመሰግኑ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይሁንና “የእኛው ለሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የተገባ ጉዳይ አልነበረም፤ ይልቁንም የቤተሰብ ምክክር መሆን ነበረበት” ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ውሕደት ያላትን ቁርጠኝነት በቃላት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ፍላጎትና በተግባር ጭምር አረጋግጣለችም ነው ያሉት።

“የአፍሪካ ቀንድ ዕድገት እና መረጋጋት በጋራ ልማታችን ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ የእኔ እና የመንግሥቴ ጠንካራ እምነት ነው፤ ሠላም እና ዕድገት ከጋራ ልማታችን የምንጋራው የትርፍ ክፍፍል ነው” ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶሃን እንዲሁም የቱርክ መንግሥት እና ሕዝብ ላደረጉላቸው የሞቀ አቀባበልና ደግነት የተሞላበት መስተንግዶ ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የቱርክ መንግሥት ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሠላም ጥረቶች ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በተለይ በራሳቸው ተነሳሽነቱን ወስደው ባለፉት ወራት በኢትዮጵያና በሶማሊያ ወንድማማች ሀገራት መካከል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ሁለት ተከታታይ ውይይቶችን ያመቻቹትን ፕሬዚዳንት ኤርዶሃንን አመስግነዋል።

እነዚህ ውይይቶች ወደ መሪዎች ደረጃ አድገው በተደረገው ምክክርም ባለፈው አንድ ዓመት በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት በሚያስችል ስምምነት መቋጨቱን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በበኩላቸው፤ የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሠላም የከፈሉትን መስዋዕትነት አይዘነጋም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በቀጣይም ሠላምን ለማፅናት በሚያደርጉት ጥረት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሃገራት የፈረሙት ሰነድ ትብብርን፣ የኢኮኖሚ እድገትንና ብልፅግናን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልፀዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም

Recommended For You