ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ሳይኖራት የወጪ ገቢ ንግዷን ከ90 በመቶ በላይ በጅቡቲ ወደብ እያከናወነች በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች፡፡ የባሕር በር አማራጮችን ማብዛት ብትችል ደግሞ ኢኮኖሚያዊ እድገቷን ከዚህም በላይ ማስወንጨፍ እንደምትችል ምሑራን ይገልጻሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ነች፤ በአሁን ጊዜ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ትገኛለች፤ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረግ የንግድ ትስስር ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር አንዱና ዋነኛው ጉዳይ የባሕር በር እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛቷና ከምትሠራው የልማት ሥራ አንጻር በርካታ እቃዎችንና ምርቶችን ታስገባለች፤ ታስወጣለች፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ የጅቡቲን ወደብ ብቻ እየተጠቀመች ፈጣን የሆነውን የኢኮኖሚ እድገት የማስቀጠሉ ጉዳይ ዋስትና አይሰጣትም፡፡ ይህንን ፈጣን እድገት ያለ በቂ ወደብ ማስቀጠል አዳጋች ስለሚሆንባት ወደ ሌሎች ሀገሮች ማማተር ግድ እንደሚላት ይናገራሉ፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና የአልሙናይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን በበኩላቸው፤ በዓለም ላይ የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው የተዳከመ በመሆኑ ለድህነት የተጋለጡ ናቸው ይላሉ፡፡ ለማሳያነትም ከሰሐራ በታች ያሉ እንደ ሴንትራል አፍሪካንና ቻድን ለድህነት አንድ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ የባሕር በር ማግኘት ከድህነት ለመውጣት ቁልፍ አማራጭ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ የባሕር በር አማራጮችን ማስፋትም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለማግኘት እንደሚያስችል ያብራራሉ፡፡
የሕዝብ ብዛት እያደገ በመጣ ቁጥር ፍላጎትም በዚያው ልክ ያድጋል የሚሉት አቶ ፍሬዘር፤ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን ፍላጎት ለማርካትና ኢኮኖሚያዊ እድገቷን ለማስቀጠል የወደብ አማራጮቿን ማስፋት ይኖርባታል ይላሉ፡፡ አማራጭ ሲኖር ተወዳዳሪነት ይጨምራል፤ ተወዳዳሪነት ሲኖር ወደቦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመጠቀም ዕድል ይፈጥራል፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ከውጭ የገባን ምርትም በዚያው መንገድ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ሲቻል የኑሮ ውድነት ጫናን መቀነስ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡
የንግድ እና የሠላም ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር ወሳኝ ናቸው ያሉት አቶ ፍሬዘር፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምታደርጋቸው የባሕር በር ስምምነቶች ለኢኮኖሚያዊ ትስስር ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሠላማዊ መስተጋብርም የሚበጁ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡
ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ እኔ በዚህ እጠቅምሃለሁ፤ አንተም በዚህ ጥቀመኝ ማለት ዓለም የሚከተለው የሠለጠነ መንገድ ነው። ይህ ለሃገራት ኢኮኖሚዊ ጥቅም ከማስገኘቱም ባሻገር ሠላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር፣ የመተባበርና የመተማመን ባሕል እንዲጎለብት እና ቀጣናዊ ትስስሮችም እንዲጠናከሩ የሚያደርግ ነው፡፡
አቶ ፍሬዘር በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል ተዋስነው ያሉት አብዛኛዎቹ ሕዝቦች ሕይወታቸው በንግድ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሀገራቱ የንግድ ትስስር ቢያደርጉ የኮንትሮባንድ ንግድን በማስቀረት ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ማስፈን እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ፡፡
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚገኙ ሃገራት የተለያየ ፀጋ አላቸው፤ ኢትዮጵያ በወንዞች የበለፀገች ነች፤ ወንዞቿን አልምታ ለጎረቤት ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደምታቀርብ ሁሉ የባሕር በር ያላቸው ጎረቤት ሃገራትም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስ ተደጋግፎ ማደግን ምርጫቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ከሚያጎለብቱ ጉዳዮች አንዱ የታሪፍ ቅናሽ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ የታሪፍ ቅናሽ ወይም ዋጋ ሌሎች ሀገሮችን ይጋብዛል፤ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ታሪፏ አነስተኛ በመሆኑና ለሽያጭ የሚተርፍ ምርት ስላላት ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መግዛትን ምርጫቸው አድርገዋል፤ የወደብ ወይም የባሕር በር አማራጮችም ሲበዙ እንደዚሁ ተመጣጣኝ ታሪፍ ለማግኘት ይረዳል፡፡ እቃዎች በጊዜው ከወደቦች ላይ ተነስተው ሳይበላሹ በሰዓቱ ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱም ያግዛል፡፡
አቶ ፍሬ ዘር ይህንኑ ሀሳብ ሲያጠናክሩ፤ ኢኮኖሚ ሲያድግ ከዓለም ጋር የሚኖረው የንግድ ግንኙነትም ያድጋል፤ የኢትዮጵያ እድገት የሚጠቅመው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ምሥራቅ አፍሪካንም ጭምር ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ ሀገራት ነፃ የንግድ እንቅስቃሴና ትስስር ማድረጉ የሚጠቅማቸው ራሳቸውን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምታደርጋቸው የባሕር በር ስምምነቶች ከቀጣናዊ የንግድ ትስስሩ አንጻር ካየናቸው ሁሉንም የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች የሚጠቅሙ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከሶማሌ ላንድ፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ የባሕር በር አማራጮችን ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ በመቀጠል የራሷንም የቀጣናውንም ማኅበራዊ ቅርርብና ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስቀጠል ላይ አልማ መሥራት ይኖርባታል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም