በሕክምና አገልግሎት ዙሪያ የሚነገሩ ማስታወቂያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- በዘመናዊም ሆነ በባሕላዊ ሕክምና አሰጣጥ ዙሪያ የሚሠሩ ማስታወቂያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አሳሰበ፡፡ ባለሥልጣኑ በጤናና ጤና ነክ ማስታወቂያ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ ባለሥልጣኑ ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ፣ ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ወደ ማኅበረሰቡ እንዲደርስ ይሠራል፡፡

ከተቀመጡ አዋጆችና መመሪያዎች ባፈነገጠ መልኩ በባሕላዊም ሆነ በዘመናዊ ሕክምና አሰጣጥ ዙሪያ የሚነገሩ ማስታወቂያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ሁሉም ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ባለስልጣኑ ለዘመናዊ ሕክምና ተቋማት ፈቃድ እንዲሁም ለባሕላዊ ሕክምናዎች ምዝገባ እያካሄደ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን እንደሚያከናውን ጠቅሰው፤ ከመጠን በላይ በሚነገሩ ማስታወቂያዎች ምክንያት ኅብረተሰቡ ላይ የተለያዩ ጉዳት እንዳያደርሱ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

በተለይ የባሕል ሕክምና ለሚሰጡ ተቋማት የምዝገባ ምስክር ወረቀት እንጂ ፈዋሽነታቸውን የሚያረጋግጥ እውቅና አይሰጥም ነው ያሉት፡፡

ሆኖም ከአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ባለሥልጣን የእውቅና ማረጋገጫ ፈቃድ እንዳላቸው አድርገው የሚያስነግሩት ማስታወቂያ ከሕግ ውጪ የሆነና ኅብረተሰቡንም የሚያሳስት በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል ብለዋል፡፡

ማስታወቂያ የሚመራበት የራሱ ሕግና መመሪያ አለው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጇ፤ ማንኛውም ከሕክምናና መድኃኒት ጋር የሚያያዙ ማስታወቂያዎች ባለሥልጣኑ ሳያውቅ መነገር የለባቸውም፡፡

ማስታወቂያዎቹም በዜናም ሆነ በፕሮግራም መልክ ሊተላለፉ እንደማይገባ ጠቁመው፤ በተለይ መድኃኒትን የተመለከተ ማስታወቂያ ማስተላለፍ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሕክምና አገልግሎት ያገኙ ደንበኞችን ምስክርነት በማስታወቂያ መልክ ማቅረብ እንደማይቻል አስታውሰው፤ የፀጉር ንቅለ ተከላና የጥርስ ሕክምና ጋር ተያይዞ ተገቢነት የሌላቸው ማስታወቂያዎች ይስተዋላሉ ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የአንድን አገልግሎት አጉልቶ የሌሎችን ተቋማት ባኮሰሰ መልኩ የሚቀርቡ ማስታወቂያዎችም ሕግን የጣሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከሕግ ውጪ የሚነገሩ ማስታወቂያዎች እንዳይነገሩና በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እየሠራ መሆኑን አመላክተው፤ ለዚህ ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘይነባ ሽኩር በበኩላቸው፤ የምግብና መድኃኒት ጉዳይ በቀጥታ ከሰዎች ሕይወት ጋር የሚገናኝ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ስታንዳርዱን የጠበቁና ትክክለኛ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የባሕል ሕክምና እንዲበረታታ ይፈለጋል ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ይሁን እንጂ የሚነገሩ ማስታወቂያዎች የተጋነኑና ኅብረተሰቡን ላላስፈላጊ ችግር የሚዳርጉ መሆን የለባቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

 አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You