አዲስ አበባ፡- በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛዎቹ የሀገሪቷ ክፍሎች ላይ የሚኖረው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ ለመኸር ሰብል ስብሰባ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስትቲዩቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መረጃ እንደገለጸው፤ በቀጣዮቹ ቀናት የሚኖረው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ የመኸር ሰብል ስብሰባና ድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራትን ለማከናወን አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡
ደረቃማ ከሆነው የእርጥበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ በተለይም በሰሜን፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በምሥራቅ፣ በመካከለኛውና በደቡብ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በአንጻራዊ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል፡፡
ይህ ሁኔታ በቋሚ ተክሎች፣ በጓሮ አትክልቶችና በመስኖ በሚለሙ ሰብሎች እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የገለጸው ኢንስትቲዩቱ፤ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በመረጃው አመላክቷል።
እንደ ኢንስትቲዩቱ መረጃ፤ በቀጣዮቹ አስር ቀናት በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ እንዲሁም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት አካባቢዎች የሚኖረው እርጥበት በተለያየ እድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበጋ ወቅት ሰብሎች፣ ለግጦሽ ሳር እና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን ይኖረዋል፡፡
ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ ሀገራችን የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ የጠቆመው የኢንስትቲዩቱ መረጃ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንደሚስተዋል ተጠቁሟል፡፡
የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለይም በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅና በደቡብ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል በጥቂት የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ የደመና ሽፋን እንደሚኖራቸው የገለጸው፤ ኢንስትቲዩቱ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በምዕራብ፣ በደቡብም ምዕራብ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ በመረጃው አመላክቷል::
አብዛኛዎቹ ተፋሰሶች ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ የሚጠበቅ ቢሆንም በጥቂት ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ያመላከተው የኢንስትቲዩቱ መረጃ፤ መጠነኛ እርጥበት ከሚጠበቅባቸው ተፋሰሶች መካከል ባሮ አኮቦ፣ በመካከለኛ እና ታችኛው ኦሞ፣ ጊቤና ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡
በአብዛኛው ዓባይ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ አይሻ፣ አፋር ደናክል፣ ኦጋዴን እንዲሁም መረብ ጋሽ ተፋሰሶች ደረቅ ሆነው የሚቆዩ መሆኑን የገለጸው ኢንስትቲዩቱ፤ በተፋሰሶቹ የሚገኘውን ውሃ ብክነትን በመቀነስ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚስፈልግ በመረጃው አመላክቷል፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም