– በአዲስ አበባ ሁለተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ተጀመረ
አዲስ አበባ፦ የልጅነት ልምሻን (ፖሊዮን) ስጋት መከላከል የሚቻለው በመደበኛነት እና በዘመቻ መልክ የሚሰጠውን ክትባት ሁሉም ሕጻናት መከተብ ሲችሉ እንደሆነ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በአዲስ አበባ ሁለተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ትናንት ተጀምሯል።
የክትባት ዘመቻው ከታኅሣሥ 3 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ተጠቁሞ፤ ክትባቱም በጤና ተቋማት፣ በቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች እና ሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሁለተኛ ዙር ልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ጤና ጣቢያ በተካሄደበት ወቅት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ እንደተናገሩት፤ በሁለተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እድሜቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ 692 ሺህ በላይ ለሆኑ ሕጻናት ይሰጣል።
ለሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ሥራም ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ 941 ቡድኖች እና ከአራት ሺህ 500 በላይ የሰው ኃይል በቀጥታ እንደሚሠማሩ ገልጸዋል።
በዘመቻው በጎ ፈቃደኞች እና ባለድርሻ አካላት በድጋፍ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተናግረው፤ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ሕፃናትን ለሞትና ለዘላቂ አካል ጉዳት የሚዳርግ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ አደገኛ በሽታ መሆኑን ተናግረዋል።
የፖሊዮ ቫይረስ ስጋት መከላከል የሚቻለው በመደበኛነት በጤና ተቋማት እና በዘመቻ መልክ የሚሰጠውን ክትባት ሁሉም ሕጻናት መከተብ ሲችሉ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ በመጀመሪያው ዙር ከመስከረም 27 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ተሰጥቷል። በዚህም 691 ሺህ 307 ሕፃናት ተከትበዋል ብለዋል።
የመጀመሪያ ዙር ዘመቻ የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላደረጉት የጤና ባለሙያዎች፣ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና የከተማዋ ነዋሪዎችን አመስግነዋል።
አሁንም የክትባት ዘመቻው የተሳካ እንዲሆንና በማኅበረሰብ ውስጥ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር ለማድረግ እንደመጀመሪያው ዙር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም