ስምምነቱ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ችግሮች እንዲፈቱ በር ይከፍታል

አዲስ አበባ፡- የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የረጅም ጊዜ ጥበቃና ልማት አስተዳደር የአጋርነት ስምምነት መፈራረሙ የፓርኩ ችግሮች እንዲፈቱ፣ በትራንስፖርትና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ተደራሽ እንዲሆን በር እንደሚከፍት የቱሪዝም ሚኒስትር ሠላማዊት ካሣ አስታወቁ፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንና በአፍሪካ 12 ሀገሮች በፓርክ ጥበቃና ልማት ላይ ከሚሠራው ‹‹አፍሪካ ፓርክስ›› በተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መካከል ነው፡፡

ስምምነቱ በተፈረመበት ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሠላማዊት ካሣ በተለይ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፤ ስምምነቱ የፓርኩ ችግሮች እንዲፈቱ የትራንስፖርትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲዘረጉለት፣ ምርምሮችና ጥናቶች እንዲካሄዱበት በር ይከፍታል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳሉት፡- አፍሪካን ፓርክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀብቶችን በማሰባሰብ ለፓርኮች ጥቅም ያውላል፤ ሥራ ይፈጥራል፤ ለብዙ ሰዎች ሥራ የፈጠረ ድርጅትም ነው፤ ያንን መነሻ በማድረግ ይህ ተቋም ፓርኩ ላይ የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራ እንዲያካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በስምምነቱ መሠረትም ፓርኩን ያስተዳድራል፤ መሠረተ ልማቶችን ይዘረጋል፤ ፓርኩ ለጎብኚዎችም ለክልሉም ለሀገርም ሀብት መፍጠር የሚቻልበት ስምምነት ነው የተደረገው ብለዋል፡፡

መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የክልሉን ማኅበረሰብ በተለይ ወጣቶችን ከፓርኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕዝቡም ፓርኩ የእኔም የሀገርም ሀብት ብሎ እንዲይዘው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ እንዲካሄድ የተደረገበት ምክንያትም ለእዚህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ስምምነቱ ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ አለው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህ ሥራ ታይቶ ሌሎች አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ስምምነቱ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችንና ለምሥራቅ አፍሪካም ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡ ለክልሉ ሕዝብ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስታውቀው፣ ትልቅ ኃላፊነትም ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

ለተግባራዊነቱ እንደ ክልል የሚጠበቅበኝን ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ ሲሉም ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ሥራው የኢትዮጵያውያንና የሀገራችን ሥራ እንደመሆኑ ፓርኩ በክልሉ ውስጥ ቢገኝም ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆነን ይህን ፓርክ ወደ ቀድሞ ገጽታው ለመመለስ መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ከሦስት እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ የመሠረተ ልማት ግንባታ እንደሚከናወን ጠቅሰው፣ ከዚያም ወደ ዋናው ፓርኩን የማልማት ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለእዚህ ሥራም የክልሉ ሕዝብ ወይም በፓርኩ ክልል ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ ትብብር ማድረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበው፣ ሥራው የሕዝቡ መሆኑን ማሳወቅ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ ከሌሎች ክልሎች ፓርኮች ጋር ሲነጻጸር ክልሉ በሙሉ ፓርክ ነው ብሎ መናገር ያስችላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ፣ ‹‹ምክንያቱም የትኛውም የክልሉ አካባቢ ብትንቀሳቀስ የዱር እንስሳ ታገኛላችሁ ብለዋል። እንስሳቱ ከሰዎች እንቅስቃሴዎች በሚመነጩ ድምፆች ሳቢያ ሊርቁ እንደሚችሉ አመልክተው፣ ይህ እንዳይሆን የእንስሳቱን አካባቢ ከሰው እንቅስቃሴ ነፃ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡

‹‹ሌላው ሠላም ነው፡፡ እኔ ወደ ክልሉ ከመምጣቴ በፊት ለተከታታይ ሁለትና ሦስት ዓመታት ግጭት ነበር፡፡ ሠላም ለማምጣት በተከናወነው ተግባር ባለፉት አራት ወራት የተፈጠረ የሠላም ችግር የለም፡፡›› ሲሉ ገልጸው፣ በቀጣይ ደግሞ ይህን ሠላምን ዘላቂ ማድረግ የመጀመሪያው ሥራ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል እላለሁ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ፣ ፓርኩን ለማስተዳደርና ለማልማት ስምምነት የፈረመው አፍሪካን ፓርክስ በደቡብ ሱዳንም እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ የዱር እንስሳቱ በሁለቱም ሀገሮች የሚኖሩ እንደመሆናቸው ሥራው በተናበበ ሁኔታ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

አፍሪካን ፓርክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ፒተር ፌርንሄድ እንዳሉት፤ ድርጅቱ ቴክኒካል፣ የፋይናንስና ፓርኩን ማስተዳደር የሚያስችል የባለሙያ አቅም በመፍጠር ለፓርኩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ለመሥራት፣ በፓርኩ አካባቢና ውስጥ የሚኖረው ማኅበረሰብ በእዚህ ሥራ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚሠራ ለትርፍ የሚሠራ ኢንተርፕራይዝ እንዲፈጠርም ይሠራል፡፡

ድርጅቱ ለፓርኩ አስፈላጊ በሆኑ የአስተዳደር፣ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች በሆኑት ሕንጻዎች እንዲሁም ተሽከርካሪዎችና አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ አተኩሮ ይሠራል፡፡

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ፣ የደቡብ ሱዳኖቹ ጊሎና ቦማ ብሔራዊ ፓርኮች በጣም ሰፊ አካባቢን የሚሸፍኑና ኩታ ገጠም መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ክልሉ በጣም ትልቅና በአፍሪካ ወሳኝ የሚባል ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፓርኮቹ በጣም የዱር እንስሳትን ጨምሮ በርካታ ብዝኃ ሕይወት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ በሀገር ደረጃ ቢካሄድም ፓርኩ ከሚዋሰናቸው ፓርኮች አኳያ ሲታይ ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር አብሮ መሥራትን የግድ እንደሚልም አስገንዝበዋል፤ ኢትዮጵያ ላይ ውጤታማ ሆኖ ደቡብ ሱዳን ላይ ድክመት ከገጠመ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያርፍ አስታውቀዋል። ሥራው ለየብቻ የሚፈጸም ቢሆንም ሁለቱ ሀገሮች በእዚህ ጉዳይ ላይ አብረው መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ኃይሉ ሣሕለድንግል

አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You