– የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድና የአውሮፓ ኅብረት የሁለቱን ሀገራት ስምምነት አድንቀዋል
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ሶማሊያ የደረሱበትን ስምምነት በፍጥነት ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ገለጹ፡፡
የሁለቱን ሀገራት ስምምነት የአፍሪካ ኅብረትና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ማድነቃቸው ተመላክቷል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ትናንት ባወጡት መግለጫ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አድንቀዋል።
ሙሳ ፋኪ ማሃማት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የደረሱበትን ስምምነት በፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መንግሥት መካከል የተደረሰውን ስምምነት እንደሚደግፍ አስታውቀዋል፡፡
የቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ሀገራቱ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ላደረጉት አስተዋፅዖም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሁለትዮሽ ጉዳያቸውን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው።
የአንካራው ሥምምነት በሁለቱ እህትማማች ሃገሮች መካከል የቆየውን ማኅበራዊ መስተጋብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ ነው ሲሉም አድንቀዋል።
የጋራ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትን እና ብልፅግናን ለማስፈን የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አስፈላጊነት አስምረውበታል።
የጋራ ፈተናዎችን በዲፕሎማሲያዊ አማራጭ መፍታት በቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ብሎም ብልፅግና ለማስፈን አዎንታዊ ፋይዳ አለው ብለዋል። ዋና ጸሐፊው የሁለቱም ሀገራት መሪዎች ላሳዩት ገንቢ ግንኙነት እና የትብብር መንፈስ አመስግነዋል።
በተጨማሪም የቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ውይይቱን በማስተናገድ እና በማሳለጥ ለተጫወቱት ወሳኝ ሚና አመስግነዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ቁርጠኝነት ዲፕሎማሲና ቀጣናዊ ትብብር ለሠላም ወሳኝ ሚና እንዳለው በተጨባጭ ያሳየ ነው ብለዋል።
አባል ሀገራት አለመግባባቶችን በውይይት፣ በአጋርነት እና በጋራ ትብብር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ኢጋድ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል።
የአውሮፓ ኅብረት የአንካራውን ስምምነት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፡- በቱርክ አደራዳሪነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ኅብረቱ በበጎ ጎኑ እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
ስምምነቱ በምሥራቅ አፍሪካ ተከስቶ የነበረውን ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ ንግግር እና እርስ በእርስ መከባበር አስፈላጊ መሆኑን ያሳየ ነውም ብሏል ፡፡
ሁለቱ ሀገራት ወደ ስምምነት እንዲመጡም የቱርክ መንግሥት ላደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚመሰገንም ነው ያስታወቀው፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም