በኦሮሚያ ክልል ከ800 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ተሰበሰበ

– በምርት ዘመኑ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን በላይ የቡና ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፡- በ2017 የምርት ዘመን ከ800 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡ በምርት ዘመኑ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን በላይ የቡና ምርት ለማግኘት መታቀዱም ተጠቁሟል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሳኒ አሚን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ከመስከረም ወር ጀምሮ የቡና ምርት የመሰብሰብ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ከመስከረም ወር እስከ ኅዳር ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስም ከ 800 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡

በክልሉ ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን የቡና ምርት እንደተገኘ አውስተው፤ በዘንድሮ የምርት ዘመን አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን ቡና ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በክልሉ የቡና ምርት ከጥቅምት መጨረሻ ወይም የኅዳር ወር አጋማሽ ሳይደርስ መሰብሰብ ተጀምሮ እንደማያውቅ በመግለጽ፤ ባለፈው ዓመት የዝናብ ስርጭቱ ያልተቋረጠ እና የአየር ፀባዩ ለቡና ጥሩ መሆኑን ተከትሎ ቡና በጊዜ ሊደርስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የቡና ለቀማ በአንዳንድ ዞኖች የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፤ አጠቃላይ እንደ ክልል የቡና መሰብሰብ ተግባሩ እስከ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እስካሁን ባለው የማሰባሰብ ሥራም ከ50 በመቶ በላይ ለመድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ለገበያ ማቅረብ ተጀምሯል፡፡ በክልሉ በመጀመሪያ የቡና ማሰባሰብ ሥራ የተጀመረው በጅማ ዞን እንደመሆኑ፤ ከዞኑ ከስድስት ሺህ ቶን በላይ የታጠበ ቡና በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ለገበያ ቀርቧል፡፡ ከጉጂ ከአንድ ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል፡፡

በክልሉ በሁሉም ዞኖች ቢያንስ አንድ የቡና አቅራቢ ማኅበር አለ፡፡ በአንዳንድ ዞኖች፣ እስከ ሦስት የሚደርሱ የቡና ማኅበራት እንደሚገኙ አመልክተው፤ ቡናን በዘመናዊ መንገድ ከመሰብሰብ አኳያም በክልሉ ከአምስት ሺህ በላይ የቡና መፈልፈያ ማሽን መኖሩን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው ዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የቡና ችግኝ መተከሉን ያስታወሱት አቶ መሐመድ፤ በዘንድሮ ዓመት በተመሳሳይ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ችግኝ በላይ ለመትከል በማቀድ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የቡና ችግኝ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው እንደሚናገሩት፤ በክልሉ መረጃ መሠረት፤ እስካሁን ያለው የክልሉ የቡና ተክል ሽፋን ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነው፡፡ በዘንድሮ ዓመት አራት መቶ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ በመትከል የማሳ ሽፋኑን ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ለማድረስ ታቅዷል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You