– የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር 550 ብቻ ነው
አዲስ አበባ ፡- የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ሀገሪቱ እየተገበረች ላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ። በኢትዮጵያ የሚገኙ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር 550 ብቻ መሆኑን ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ሀገሪቱ ተግባራዊ እያደረገች ለምትገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት የሚያግዝ ነው።
እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ እንደ ሀገር ያለንን የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር የሚጨምር ነው። ይህም የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የካፒታል ገበያ ወደ ሥራ ሲገባ በሀገራችን ለሚመጡ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የኢንስቲትዩቱ መቋቋም ትልቅ ፋይዳ አለው።
ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ አዳዲስ የውጭ ሀገር ባንኮች የሰው ኃይል ለማቅረብ ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎች አስፈላጊ መሆናቸው ገልጸው፤ በገበያው ላይ ተወዳዳሪ እና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ማግኘት ካልተቻለ የሥራ እድሉ ለሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች ይሰጣል። ይህም ሀገሪቱ ልታገኝ የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ያሳጣታልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች ዋነኛው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ሥርዓትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ባለው መልኩ መዘርጋት ፣ የሂሳብ አያያዝ ሪፖርት አገልግሎትን ጥራት ማስጠበቅ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት በዘርፉ ለመሥራት የሚፈልጉ ባለሙያዎችን ተቀብሎ የሚያሰለጥን መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ፤በሀገር ውስጥም ሆነ በሌሎች ሀገራት ለመሥራት የሚያስችል እድል እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሚያዘጋጀው ስልጠና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች እና የትምህርት ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት የሀገሪቱን የታክስ ሕግ ሥርዓትና የንግድ ሕግ የሚያካትት መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል ።
ኢንስቲትዩቱ ሲቋቋም እንደ ሀገር የሚያስፈልገውን ብቁ እና በቂ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር ለማፍራት የሚያስችል እንደሆነ አመልክተው፤ ስልጠናውን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች መውሰድ ለሚፈልጉ ምቹ በሆነ መልኩ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ኢንስቲትዩቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት የማጠናከሪያ ትምህርትና የመፈተኛ ጣቢያዎችን እንደሚያዘጋጅም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር 550 ብቻ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህ ቁጥር ካለው የሕዝብ ቁጥር እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር እጅግ አናሳ መሆኑንም ገልጸዋል።
የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር ማነስ ምክንያት ስልጠናው በሀገር ውስጥ የማይሰጥ መሆኑን እና ስልጠናውን የሚሰጡ የውጭ ተቋማት የሚጠይቁት ከፍተኛ ክፍያ እንደሆነ አመልክተዋል።
የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ረቂቅ አዋጁ በበጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ውይይት እንዲደረግበት ተመርቷል ነው ያሉት ።
ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ሰልጣኞችን የሚቀበልበት መስፈርት እና መመሪያዎች የሚኖሩት ሲሆን፤ ብቁ እና በቂ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ለማፍራት የሚያስችል ነው ሲሉ አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም