የሰላም ግንባታ ፕሮጀክቱና የክልሎቹ አጋርነት

ዜና ሀተታ

ተምኪን ይሀ ትባላለች። በወርልድ ቪዥን እና በአውሮፓ ህብረት ትብብር በሶስት ክልሎች በአማራ፣ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉምዝ የሚካሄድ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ የማድረጊያ መርሀ ግብር ላይ የአማራ፣ የትግራይና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ወክለው የስዕል ስራቸውን ካቀረቡ ታዳጊዎች መካከል አንዷ ናት። ይች ታዳጊ የአማራ ክልል ህፃናትን ወክላ የስዕል ስራዋን ያቀረበች ናት።

በመርሀ ግብሩ ላይ ይዛ የቀረበችው ስዕል አንዲት በፈገግታ የተሞላች ተማሪ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ስትማር የሚያሳይ ነው። ብዙ ሰዎች ስለ ሰላም ሲነሳ ቀድሞ በአእምሮአቸው የሚመጣው የነጭ እርግብ ምስል ነው የምትለው ተምኪን፤ እርሷ ግን ሰላምን ለመግለፅ የተማሪ ስዕል መሳሏ በብዙ ምክንያቶች መሆኑን ትገልፃለች።

ከእነዚህ ምክንያቶች ጥቂቶቹም እሷ ባላት መረጃ በክልሉ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በሰላም እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው መገኘታቸው፣ ከዛ በተጨማሪም በሰላም እጦት ምክንያት ብዙ የኢኮኖሚ ችግር እየደረሰባቸው በመሆኑ እንዲሁም በተለይም ሴት ተማሪዎች ፆታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ታብራራለች።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ የሆኑት ዶክተር ጥላሁን መሀሪ በበኩላቸው፤ ሰላም የሁሉ ነገር መገለጫ መሆኑን ገልፀው፤ እንደ አማራ ክልል የሰላም አጀንዳ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ይጠቁማሉ።

የሰላም አጀንዳ ወቅቱ የሚፈልገውና መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑን የሚገልፁት ተወካዩ፤ የአማራ ክልልም በልዩ ትኩረት እየሰራበት እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በሰላም ጉዳይ ላይ እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም ከፕሮጀክቱ አጋሮች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በዙም ባስተላለፉት መልዕክት ጊዜያዊ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክቱ ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይገልፃሉ። የትግራይ ሕዝብ ባለፉት ዓመታት ያሳለፈውን ጦርነት ተከትሎ ከመጡ ብዙ ቀውሶች አኳያ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክቱን በቀላሉ ልናየው አንችልም  ይላሉ።

ከሰላም የሚበልጥ ሥራ የለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ፕሮጀክቱን ማስቀጠልና ዘላቂ ሰላም ማምጣት ትልቅ የቤት ስራችን ነው ብለዋል። የክልልና የፌዴራል መንግሥት አመራሮችም ይህንን የሰላም ጉዳይ በማስቀጠሉ ረገድ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልፀዋል።

ሰላም ከውስጥ የሚፈጠር ነው ያሉት ደግሞ የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ ናቸው። እንደእርሳቸው ገለፃ፤ አብዛኞቹ የሰላም እጦት ዋነኛ መንስኤዎች ከእምነትና ከባህል መነጠል ጋር ተያይዘው የሚመጡ ናቸው። በተለያየ ጊዜ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ያለው ተሰሚነት እየተሸረሸረ በመምጣቱም ከፍተኛ የሰላም እጦት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።

ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት የሰላም እጦት እንደነበር ያስታወሱት ተወካዩ፤አሁን ላይ ግን የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማስተባበር በተደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ሰላም የተፈጠረበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።

ቀጣዩ ሥራ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት አጠናክሮ እየሰራ በመሆኑ ለሰላም ግንባታ ፕሮጀክቱ የሚፈለገውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ክልሉ ዝግጁ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

የሰላም ግንባታ ፕሮጀክቱ በሶስቱ ክልሎች ማለትም በአማራ ፣ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች መተማመንና ተግባቦት ላይ ተመስርቶ ሰላምን መልሶ ለማምጣት ያለመ መሆኑ በመርሀ ግብሩ ላይ ተጠቁሟል።

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You