አዲስ አበባ፡– ሙስና የሀገርን እድገት የሚያደናቅፍና የቀጣይ ትውልድ ከድህነት የመውጣትን ተስፋ የሚሰብር ደዌ ስለሆነ ወጣቱን ዋነኛ ተዋንያን ያደረገ የፀረ ሙስና ትግል ማድረግ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል፤ የነገን ስብእና ይገነባል!’’ በሚል መሪ ሀሳብ 21ኛው የዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን አስመልክቶ ትናንት የማጠቃለያ መርሀ ግብር ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የሙስና ወንጀል በኢትዮጵያ የቆዩ ማህበራዊ ጥሪቶችን የሚያሽመደምድ፣ የሀገርን እድገት የሚያደናቅፍ ብሎም የቀጣይ ትውልድ ከድህነት የመውጣት ተስፋን የሚሰብር ደዌ ነው፡፡ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ወጣቱን ዋነኛ ተዋንያን ያደረገ የፀረ ሙስና ትግል ማድረግ ይገባል፡፡
ወንጀሉ ከሚያስከትለው ውስብስብ ችግር አንጻር በመደበኛ ክስ እና ምርመራ ለመፍታት ቀላል አለመሆኑን ገልጸው፤ በተቋማት ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራርን በመዘርጋት የሙስና ወንጀልን በዘላቂነት መከላከል እንደሚገባ አመልክተዋል። የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎቻቸው ጠንካራ ግብረ ገብና ሥነምግባር በማስተማር ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ በስሜት የማይነዳ፣ ማህበራዊ ኃላፊነት የሚሰማውና ሙስናን የሚፀየፍ ዜጋ የመቅረጽ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወጣት ዜጎች በየዘርፉ በብዛት በመሪነት ደረጃ ካሉባቸው ሀገራት ውስጥ የምትጠቀስ መሆኑን አንስተው፤ ከሙስና የፀዳና የበለፀገ ሀገር ለመገንባት ወጣቱን ያማከለ የዘመነ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
ቤተሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችም የወጣቱን ልቦና ታማኝ፣ ኃላፊነት የሚሰማውና በፍትሐዊነት የሚያምን አድርጎ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ሙስናን አምርረን በመከላከልና በመታገል የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ማድረግ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሚዲያ አካላት ያላቸውን ኃያልነት በመጠቀም በሙስና ስጋት ዙሪያ ግንዛቤ በመስጠትና ለፀረ ሙስና ትግል ወጣቱን ዋነኛ ተዋንያን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ፍትሐዊ ማህበረሰብ ያለው ትውልድ መፍጠር ለነገ የሚተላለፍ ሥራ አለመሆኑን አንስተው፤ ሁሉም ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመገንባት ወጣቶች ላይ በርትቶና ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል። ወጣቱ ትውልድም ቀጣይነት ባለው መንገድ በፀረ ሙስና ትግል ላይ ብርታትና ተጋድሎን በማጠናከር መታገል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሙስና በሀገር ህልውና ላይ አደጋ የሚደቅን የጋራ አጀንዳ ነው፡፡ የዘንድሮ ፀረ ሙስና ቀን ሲከበርም ትውልዱ ሙስና አትራፊ እንዳልሆነና ዘላቂ መፍትሄ መሆን እንደማይችል የሚገነዘብበት ብሎም ሙስና በሀገር ዕድገትና ልማት የሚያስከትለው አስከፊነት በተሻለ መልኩ እንዲረዳ የተሻለ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ በርካታውን ድርሻ የሚይዙት ወጣቶችን በሥነ ምግባር በማነጽ ለኢትዮጵያ ብልፅግና ጉዞ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ረገድ ትምህርት ተቋማት፣ቤተሰብና ማህበረሰቡ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡የፀረ ሙስና ትግል አስቸጋሪና ቁርጠኝነትን እንደሚፈልግ ገልጸው፤ ሁሉም አካል የፀረ ሙስና ትግሉን በጽናትና በኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡
ለፀረ ሙስና ትግል ውጤታማነት ሙስናን ከመከላከል በተጨማሪ የሕግ ማስከበር፣ የምርመራ ሥራና ፍርድ አሰጣጥ ፣ ሀብት የማስመለስ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለዚህም ቁርጠኛ አመራርና ተቋማት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም