በትግራይ ክልል የወባ በሽታን የመከላከል ሥራ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል ለሚካሄደው የወባ በሽታን የመከላከልና መቆጣጠር ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በትግራይ ክልል በሮማናት፣ ማይቅነጣል፣ ዕዳጋ ዓርቢና ሐውዜን ከተሞች የሚገኙ የጤና ተቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ ትናንት ተመልክቷል።

የጤና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች የጤና ተቋማትን በአካል ተገኝተው በማየታቸው የሥራ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው የክልሉ የጤና ባለሙያዎች ገልፀዋል።

የወባ በሽታን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች የፀረ ወባ ኬሚካል፣ የአልጋ አጎበርና መድኃኒት እንዲሟላላቸውም ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት፤ እንደ ሀገር የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው ወደ ትግራይ ክልል የመጣነው የወባ በሽታን ለመከላከል የተሰጠው ፈጣን ምላሽ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የጤና ባለሙያዎችና በየደረጃው ያለው አመራር በሽታውን ለመከላከል ቅድሚያ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ለማየትና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመመልከት ነው ብለዋል።

በዚህም ክልሉ በሽታውን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አድንቀው፤ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዝበዋል።

በተለይ የጤና ባለሙያዎች ችግሮችን ተቋቁመው ማህበረሰቡን በማስተማር ቤት ለቤት የሚሰጡት የምርመራና የሕክምና ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ የሚያጋጥሙ የፀረ ወባ ኬሚካል እና አጎበር እጥረትን ለማቃለል መንግሥት ግዥ እየፈጸመ መሆኑን አንስተው፤ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልል የተጀመሩ የወባ በሽታ የመከላከል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አማኑኤል ኃይለ በበኩላቸው፤ በከፍተኛ ሁኔታ የታየውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ፈጣን ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁንም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተጨማሪ ጥረት እንደሚያስፈልግ ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የመድኃኒት እና የላብራቶሪ ግብዓቶች አቅርቦት እየተሻሻሉ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ተጨማሪ የፀረ ወባ ኬሚካልና የአልጋ አጎበር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You