ዘመኑን የዋጀው የዲጅታል ትምህርት ጉዳይ

ዜና ትንታኔ

መንግሥት ዲጅታል ትምህርትን የትምህርት ስብራት ማቃኛ ስልት አድርጎ ወደ ትግበራ አስገብቷል። ይህ የዲጅታል ትምህርት ችግሮችን ከመፍታት፣ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥና ቴክኖሎጂን ከማስፋፋት አንጻር ምን ፋይዳ አለው? ስንል የዘርፉን ምሁራን አነጋግረናል።

ካሳሁን ገላ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ተጠሪ ናቸው። የዲጅታል ትምህርት ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ። ዋነኛ ዓላማና ግቡ የመማር ማስተማር ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ መደገፍ መሆኑን ይገልጻሉ። ከዚህ የተነሳም ዲጅታል ትምህርት እውቀት መገብያ ፣ ብቁ፤ ተወዳዳሪ፤ ፈጣሪና ችግር ፈቺ የትምህርት ማህበረሰብ መፍጠሪያ መሆኑን ያስረዳሉ።

የዲጅታል ትምህርት ለትምህርት ማህበረሰቡ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን የሚያስረዱት ኃላፊው፤ ትምህርቱ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የትምህርታቸውን ይዘት ደጋግመው እንዲያነቡ የሚያስችል፤ ይዘቶቹ ስዕላዊና ምስል ከሳች በሆነ መልኩ በቀላሉ እንዲረዱት የሚያደርግ፤ የማስታወስ ችሎታን  የሚያሳድግ ነው። እንዲሁም ከውጭው ዓለም ጋር በእኩል ለመራመድ የሚያስችል መሆኑን ያብራራሉ።

እንደ ካሳሁን (ዶ/ር) ገለጻ፤ የትምህርት ስብራት የሆነውን የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በኩልም ሚናው ቀላል አይደለም። የትምህርትን ተደራሽነት በማስፋት ይዘቶችን፤ የማስተማር ዘዴዎችን በቀላሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማድረግ ያስችላል። ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የኢኮኖሚ አቅማቸውን እያሳደጉ የተሻሉ እውቀቶችን የሚጨብጡበት እድል ይፈጥርላቸዋል። ተማሪዎች ከትምህርታቸው  ጎን ለጎን የራሳቸውን ገቢ እያመነጩ የቀጣይ እጣ ፋንታቸውን የሚያመቻቹበትና የሥራ እድላቸውን የሚያሰፉበት ነው ይላሉ። በተጨማሪም ሁሉም የትምህርት ማህበረሰብ ከተለያዩ ወንጀሎች እንዲጠበቁ፤ የተሻለ እውቀትን እንዲቀስሙ፣ የተመረጡና ለእነርሱ የሚሆኑትን ይዘቶች ለይተው እንዲከታተሉም እድል ይሰጣል ነው ያሉት።

ፕሮፌሰር አበባው ይርጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸውም ካሳሁን (ዶ/ር) ሃሳብ በማጠናከር ነው የሚናገሩት። ዲጅታል ትምህርትን አሁን ላይ ስለወደድነው ብቻ የምንከተለው ጉዳይ አይደለም። ተገደን የምንገባበት ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ተቀምጠን ተወዳዳሪ፣ ብቁ፣ ተመራጭና ከዓለም ጋር እኩል የምንራመድ ካልሆነ ለብዙ ችግሮች እንጋለጣለን። ከዚህ አኳያም ዘመኑን ሊዋጅ የሚችለውን ዲጅታል ቴክኖሎጂ መጠቀም ግድ ይለናል።

ፕሮፌሰር አበባው፤ አሁን የትምህርት ማህበረሰቡ ተለዋዋጭ እና ፈጣን የሆነው ቴክኖሎጂ ላይ መገኘት ግድ መሆኑን ይናገራሉ። ዲጅታል ትምህርትን ተግባራዊ ማድረግ የሀብት ብክነትን መቀነስ፣ አሰራርን ማዘመን፣ ተጨባጭ እውቀትን ማምጣትና ተወዳዳሪነትን መጨመር ነው። ትምህርት ለሁሉም የሚለውን መርህ ከዓለም ጋር በእኩል ለመራመድ እውን እንደማድረግም ይቆጠራል ይላሉ።

በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ወጣት ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ይልቅ ምርጫውን በቀላሉ ሊረዳውና ሊገባው የሚችለው የዲጅታሉን ዓለም ላይ የተመሰረተ ነው። ትምህርት በዲጅታል መልኩ መስጠት አዋጭነት አለው። የዲጅታል ትምህርት ተደራሽነት፤ ፍትሃዊነትና ተወዳዳሪነት እንዲሁም በአዳዲስ የፈጠራ ሥራ የሚታወቁ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል በመሆኑ ይሄንን መጠቀም የውዴታ ግዴታ መሆኑን ያስረዳሉ።

ካሳሁን(ዶ/ር)፤ ዲጅታል ትምህርት በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ቢታመንም ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን ስለሚጠይቅ በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ ያስቸግራል ብለው ያምናሉ። ከዚህ አንጻርም አቅም በፈቀደ የሚሰራበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ይገልጻሉ። ደረጃ በደረጃ የሚሰራበትንና ወደ ቴክኖሎጂው ሊያንደረድሩ የሚያስችሉ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባም ይጠቁማሉ።

የዲጅታል ትምህርትን ለማስፋፋት ትልቅ ማሰብ ብቻ በቂ እንዳልሆነ የሚናገሩት ካሳሁን (ዶ/ር)፤ የቤተሙከራ ደረጃዎችን ማሻሻል፣ የዲጅታል ፓርኮችን ማስፋፋት፣ ወጣቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ በስፋት መስራት በቀላሉ ያሉትን ችግሮች ከሚፈታባቸው መንገዶች መካከል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ተማሪዎች በኮምፒውተሮችና ሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጮች በቀላሉ ተጠቅመው እርስ በእርስ የሚረዳዱበትን ሥርዓት መፍጠር፣ ከስማርት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ትምህርቶችን ኔትዎርክ ካለባቸው አካባቢዎች ወደ ሌለባቸው ትምህርት ቤቶች ማጋራት፤ የሳይበር ክበቦችን ማቋቋም፤ ከዲጅታል ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት እንደሚገባም ይናገራሉ።

ፕሮፊሰር አበባው በበኩላቸው፤ ዲጅታል ቴክኖሎጂ ለማንኛውም እንቅስቃሴ መሰረታዊ ነገር መሆኑን ይጠቅሳሉ። በመጀመሪያ አደረጃጀትን በመፍጠርም አቅም ያላቸውን ሰዎች ወደ ፊት በማምጣት ትምህርቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። እውቀቱና ክህሎቱ እንዲዳብርም ወጣቶችንና በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ከማነቃቃትና ከመደገፍ አንጻር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ያነሳሉ።

ዲጅታል ትምህርትን እንደ ሀገር በውድድር፤ በፈጠራና በመረዳት ላይ ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው። በአዲስ አሰራሮች እየረቀቀ እንዲሄድ ሆኗልም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ከመዝናናት ባለፈ ትምህርት ነክ ጉዳዮችን እንዲከውኑ እድል አግኝተዋል።

ሁለቱም ምሁራን ዲጅታል ትምህርት የሁሉንም ሙያ መሰረት የሚያሳልጥ ነው። በአግባቡ መተግበር ከተቻለ የሀገር ልማት ስራዎች በሁሉም ዘርፍ የተሳካላቸው ይሆናሉ። የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነትና ዓለም አቀፋዊነት በቀላሉ ይረጋገጣል። ፈጣሪ ትውልድ ይፈጠርና ሀገርን ከምትፈልገው የእድገት ማማ ላይ እንድትደርስ ያደርጋታል ሲሉ ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You