“በአማራ ክልል ግጭቶች ባልነበሩባቸው ጊዜያት ከሚደርሰው የበለጠ ማዳበሪያ አድርሰናል”-ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ሚኒስትር

አዲስ አበባ፦ አምና በአማራ ክልል ግጭቶች ባልነበሩባቸው ጊዜያት ከቀረበው የበለጠ ማዳበሪያ አድርሰናል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡ ምርጥ ዘርን በተመለከተ  በሁሉም አካባቢ እጥረት መኖሩን አመለከቱ።

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ እንደ ግብርና ሚኒስቴር ግጭት ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ የግብርና ግብዓቶችን ማድረስ ይጠበቅብናል ብለዋል። በዚህም አምና አማራ ክልል ተደራሽ ያደረግነው ማዳበሪያ እስካሁን በክልሉ ግጭቶች ባልነበሩባቸው ጊዜያት ከሚደርሰው ማዳበሪያ የበለጠ ማድረስ የቻልንበት ጊዜ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ማዳበሪያ ለማድረስ የተከፈለው ዋጋ ቀላል አለመሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ማዳበሪያውን በማጓጓዝ ወቅት በጸጥታ ኃይል እጀባ እየተደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል። ለዚህ ዋና ምክንያቱ አርሶ አደሩ ማረስና መዝራት ስላለበት እንደሆነ ገልጸው፤ ካላረሰና ካልዘራ ግን እንደ አርሶ አደር መውደቅ፤ ቀጥሎም እንደ ሀገር መውደቅ ስለሚመጣ ነው ብለዋል።

ከዚህም የተነሳ ወደ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ዘንድ አድርሰናል ያሉት ግርማ (ዶ/ር)፤ ይህ ከዚህ በፊት በአራት ክልል በየትኛውም ጊዜ ተደርጎ የማይታወቅ ቁጥር ነው ሲሉ አስረድተዋል። ማዳበሪያውን ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በእጀባ ጭምር ማድረስ መቻሉንም አመልክተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ አማራ ክልል ማዳበሪያ ሲዘረፍ ነበር። በሚሊዮን የሚቆጠር ማዳበሪያ መንገድ ላይ ተዘርፏል። ይሁንና ድርጊቱ ማዳበሪያን ከማድረስ አላገደንም። ግብዓቱ አርሶ አደሩ ዘንድ የግድ መድረስ ስላለበት ያንን አድርገናል። ያም በመሆኑ ዘንድሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የምንጠብቀው ምርት ከፍተኛ ነው። በቅርቡ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር አቅንተን በነበረበት ወቅት ለማመን የሚከብድ ምርት ለማየት መቻላችን አንዱ ማሳያ ነው።

በሌላ በኩል የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደተፈረመ፤ በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን መጋዘን ውስጥ የነበረውን ማዳበሪያ መጀመሪያ መጫን የጀመርነው ወደ ትግራይ ነው። በዚህም በ2015 ዓ.ም 700 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ለትግራይ አቅርበናል ብለዋል። ለእነሱ ተገዝቶ እስኪቀርብ ድረስ ጊዜው እንዳያልፍ እና አርሶ አደሩ ወደ ሥራ እንዲገባ ወደትግራይ ክልል የላክነው ወዲያው ነው ሲሉ ተናግረው፤ በ2016 በጀት ዓመትም ወደ 800 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ለክልሉ መላኩንም አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ፣ ምርጥ ዘርን በተመለከተ ሁሉም ዘንድ እጥረት አለ ሲሉ ጠቅሰው፤ ለእሱም ቢሆን በመፍትሔነት በትግራይ ክልል ያደረግነው ነገር እዚያው ምርጥ ዘር በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እንዲባዛ ማድረግ ነው ሲሉ አስረድተዋል። ከአምና ጀምሮ በስፋት እየተሰራበት መሆኑንም ገልጸው፤ ችግሩ በቀጣዩ ዓመት የበለጠ እንደሚቃለልም አመልክተዋል።

ትግራይ ክልልን ጨምሮ የአምና የበልግ እቅዳችንን መቶ በመቶ መስራት ችለናል። የዘንድሮን መኸር ማረስ ያቀዱትን ያህል መሬት የሸፈኑበትና በጣም የተሻለ የሚባል የሰብል ቁመና ያለበት ጊዜ ነው ብለዋል ።

አርሶ አደሩ ግብዓቱን ሲያገኝ እንደማንኛውም ሌላ አካባቢ ስራውን የሰራበት ሁኔታ አለ። አሁን ያንን ምርት የመሰብሰብ ስራዎች ላይ ተጨማሪ ድጋፍ እየተደረገ፣ የጸጥታ አካላት ጭምር እያገዙ ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በ2010 በጀት ዓመት በዋና ዋና ሰብሎች የተመረተው 306 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነው። በ2016 ደግሞ 507 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማምረት ተችሏል። በዚህ በአምስት ዓመቱ 200 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት ተመርቷል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ መናገራቸው ይታወሳል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You