አዲስ አበባ፡- ራስ ገዝ መሆን ማለት ሀብታም ብቻ የሚማርበት ድሀው ትምህርት የሚነፈግበት ሳይሆን ዩንቨርሲቲዎች ትክክለኛ የእውቀት ማመንጪያ እንዲሆኑ በነፃነት የሚያስቡበት ሂደት መፍጠር እንደሆነ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል የሱፍ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጀማል የሱፍ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሆኑ ማለት ሀብታም ብቻ የሚማርባቸው ድሀው ትምህርት የሚነፈግባቸው እንዲሆኑ ማድረግ አይደለም፡፡ በዚህ ዙሪያም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል፡፡
ራስ ገዝ መሆን ማለት የአስተዳደራዊ ነፃነት ነው እንጂ ከመንግሥት መነጠል ማለት አይደለም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከሌላው ጊዜ በበለጠ የመንግሥትን እገዛና ድጋፍ እንደሚፈልግም ገልጸዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የብዙ መሰረተ ልማቶች እጥረት የሚታይባቸው ከመሆኑ አኳያ የመንግሥት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ ራስ ገዝ ይሆናሉ ከተባሉት ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ላይ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
ከዝግጅቶቹ አንዱ የሕግ ማሕቀፎችን መከለስ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በትምህርት ሚኒስቴር፣ አሜሪካን ኤምባሲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እገዛ ስትራቴጂክ ዕቅዱንና የሴኔት ሕጎቹን እየከለሱ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ምን አይነት የሕግ ማሕቀፍ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ እንዳለም ጠቁመው፤ ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ በሚሆንበት ጊዜ የሚያስፈልጉትን ፖሊሲዎች ለማዘጋጀት ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን እየከለሱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሀብትን ከማሰባሰብ አኳያም ለዩኒቨርሲቲው ጥሩ የገቢ አቅም ሊሆን ይችላል ለምንለው የተለያየ ዘርፍ ኢንተርፕራይዝ መመሪያው በቦርድ ፀድቆ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ከፕሮግራሞች ጋር በተያያዘም ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ በተልዕኮ መለየቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ የቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች እንዲሁም የምርምር ትኩረታችን በምን መልኩ መሆን እንዳለበት እየተገመገሙ እንዳለ አስረድተዋል፡፡
ራስ ገዝ በሚሆንበት ጊዜ እንደ ሀገር የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክተው፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የትምህርት ብድር የሚከፍሉበት የአሰራር ሥርዓት ከወዲሁ አለመዘረጋቱ ለዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን አንዱ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በሌላው ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ይዘው ወደ ፋይናንስ ተቋማት ከሄዱ ተቋማቱ ውጤታቸውን በማየት የሚፈልጉትን ብድር እንደሚሰጡአቸው ገልፀው፤ ያን ብድር ትምህርታቸውን አጠናቀው ስራ ሲይዙ እንደሚከፍሉ አስረድተዋል፡፡የዚህ አይነት ምቹ የአሰራር ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ ራስ ገዝ የመሆኑን ሂደት ሙሉ በሙሉ መሬት ለማስያዝ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
መንግሥት የመክፈል አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ እንደ አንድ አቅጣጫ መያዙን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ እነዚህን ተማሪዎች ለመለየት የሚያስችል መንገድ አለመኖሩም ራስ ገዝ ለሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ሌላኛው ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በሌላው ዓለም የዜጎች ሀብት ተመዝግቦ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በእኛም ሀገር መክፈል የሚችሉና የማይችሉትን ለመለየት የሚያስችል ሁኔታዎችን ከወዲሁ መፍጠር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ገቢን በራሳቸው እንዲያመነጩ ከማድረግ አኳያ ከምርምር ውጤቶችም እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸው፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማሕቀፍ አለመኖሩም ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር አንፃር ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ህብረት እና በሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት የሚደገፉ ዓለምአቀፍ ፕሮግራሞችም እንዳሉት አስረድተዋል፡፡ ሰፋፊ የመማሪያና የምርምር ማስኬጃ ቦታዎች እንዳሉትም አስታውሰዋል፡፡
በምርምርም የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገቡና ችግር ሊፈቱ የሚችሉ በግብርና፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች ዓለምአቀፍ ምርምሮችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችል ደረጃ ላይ እንዳለ ገልጸው፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ዝግጅቱ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ራስ ገዝ ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ በሚሆንበት ጊዜ አሁን ካለው በበለጠ ስራውን የሚሰራበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም