አዲስ አበባ፦ 57 ተማሪዎችና 121 የዩኒቨርሲቲ መምህራን ነጻ የትምህርት ዕድል (ሙሉ ስኮላርሽፕ) አግኝተው ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መሄዳቸውን በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ የፕሬስና መረጃ ኃላፊና የራስመስ ስኮላርሽፕ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ከበደ ገለጹ::
አቶ ሰለሞን ከበደ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አስር የአውሮፓ ሀገራት ኤምባሲዎችና የትምህርት ተቋማት ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል አቅርበዋል:: ይህ መርሐ ግብር ወደ አውሮፓ ሄደው መማር ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት በአውሮፓ ህብረት ራስመስ ፕላስ ስኮላርሽፕ ፕሮግራም 57 ተማሪዎች ሙሉ ስኮላርሽፕ አግኝተው ወደ አውሮፓ ሄደው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤እንዲሁም 121 የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲሁ ወደ አውሮፓ ሀገራት ሄደው ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል:: ይህ ለኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ አውሮፓ ሀገራት የሄዱ የዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በትርፍ ጊዜያቸው እንዲያስተምሩም ምቹ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን የገለጹት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ኢትዮጵያ ካላት ኢኮኖሚ አንፃር በሁሉም ሀገራት ዜጎቿን ልካ በክፍያ ማስተማር አትችልም፤ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለያዩ የውጭ ሀገራት ነፃ የትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻል ትብብር መፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
ብርሃነመስቀል (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ እነዚህ ሀገራት ተጉዘው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ጥረት እያደረገ ነው:: በተለይ ተማሪዎቹና የሀገራቱ ኤምባሲዎች የሚገናኙበትን መድረክ በማመቻቸት ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ነው:: የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይህን መድረክ በማዘጋጀትም የኤምባሲ ተወካዮች የትኞቹ የስኮላርሽፕ አይነቶች በየሀገሮቻቸው በነፃ የትምህርት ዕድል እንደሚሰጡ ግልፅ ማብራሪያ ይሰጣሉ::ይህም ለነጻ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚዎች መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል::
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር አቅምና ችሎታው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የስኮላርሽፕ ዕድል እንዲያገኙ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊን ከኤሜኤስበርገር በበኩላቸው፤ መርሐግብሩ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የትምህርት ልማት ትብብር የሚያሳይ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ባሉ ሀገራት ነፃ የትምህርት ዕድል ማግኘት እንዲችሉ ግልፅ ማብራሪያ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በትምህርትና ስልጠና በማብቃት የወደፊቷን የኢትዮጵያ መሪዎች ለማፍራት ድጋፍ ያደርጋል ያሉት አምባሳደር ሶፊን ከኤሜኤስበርገር፤ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩን በመጠቀም በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል እንደሚያገኙ እምነት አለኝ ያሉት አምባሳደሯ፤ የአውሮፓ ህብረት በተለያዩ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም