አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሶስት ወራት ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ::
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ፍቅሬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማው በ2017 የበጀት ዓመት ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ከታቀደው ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ብቻ 14 ትላልቅ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል:: በዚህም አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ተመዝግቧል:: ለአንድ ሺህ 400 ሰዎችም የሥራ ዕድል ተፈጥሯል::
በበጀት ዓመቱ 45 ከፍተኛ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ግብርና እንዲሁም በአገልግሎትና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ይሰማራሉ ተብሎ ዕቅድ ስለመያዙ አውስተው፤ በእቅዱ መሰረት አራት ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማስመዝገብና ለሁለት ሺህ 500 ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ተናግረዋል:: የሩብ ዓመቱ አፈጻጸምም የታቀደውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል እንደሆነ ያመላክታል ብለዋል::
በከተማው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መሰረተ ልማቶች የለማ 103 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ተዘጋጅቶ እንደተቀመጠ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከዚህ ውስጥ 35 ሄክታሩ ለኢንዱስትሪ፤ 55 ሄክታሩ ለከተማ ግብርና እንዲሁም የተቀረው በሆቴሎችና በተለያዩ የቱሪዝም ዘርፎች ለሚሰማሩ ፕሮጀክቶች የሚውል እንደሆነ ጠቅሰዋል::
በበጀት ዓመቱ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ሥራ ከማስገባት ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም የመንግሥትን መሬት ወስደው ሳያለሙ በቆዩ ፕሮጀክቶች ሕግ የማስከበር ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል:: በዚህም 24 ፕሮጀክቶች በውላቸው መሰረት ሥራ እንዲጀምሩ ምክርና ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ወደ ልማት መግባት ባለመቻላቸው በኢንቨስትመንት አዋጅ መሰረት ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዙ መደረጉንም ጠቁመዋል::
እንደ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ገለጻ፤ ከተሰረዙት 24 ፕሮጀክቶች 15 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት በአሁኑ ጊዜ ወደ መሬት ባንክ ተመልሶ ለሌሎች አልሚዎች ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው::
መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ የአምራቹ ዘርፍ የብድር አቅርቦት ሁኔታ መሻሻል እያሳየ ቢሆንም መሰረታዊ የብድር ጥያቄዎች ምላሽ መዘግየት፤ ከዶላር ጋር በተያያዘ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት መከሰት፣ ባለሀብቶች በሚፈልጉት ጊዜና ሁኔታ ወደ ሥራ እንዳይገቡ በተወሰነ መልኩ ተግዳሮት ስለመፍጠሩም ኃላፊው አመላክተዋል::
ሀዋሳ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሰረተ ልማት ያላትና አስተማማኝ ሰላም ያላት ናት ያሉት ኃላፊው፤ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በከተማዋ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱና በሚፈልጉት የሥራ ዘርፍ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል::
በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችም በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ራሳቸውንም እንዲለውጡ፤ አካባቢውንም እንዲያለሙ አቶ ታደሰ ጥሪ አቅርበዋል::
አምሳሉ ፈለቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም