አዲስ አበባ፡- በሦስት ዓመታት ውስጥ ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሻይ ቅጠል ለማልማት እየተሠራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ክልሉ ለሻይ ቅጠል ምርት ተስማሚ ነው፡፡ በሦስት ዓመታት ውስጥ ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሻይ ቅጠል ልማት ለመሸፈን እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡ለዚህም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የማሳ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ልየታ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለችግኝ ዝግጅት የሚውሉ የችግኝ ጣቢያዎችን የማቋቋም፣ ውሃና ሌሎችም አስፈላጊ ግብዓቶችን የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ በጅማ፣ ኢሉ አባቦራ እና ቡኖ በደሌ ዞኖች ላይ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኘም ገልጸዋል፡፡
በሂደቱ ከፍተኛ ልምድ እየተገኘበት ማህበረሰቡም በሰፊው እየተሳተፈበት መሆኑን አመላክተው፤ በቀጣይ ዓመታት ዘርፉ ጥሩ ውጤት ይመዘገብበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እቅዱን ለማሳካትም ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው አመራርና ባለሙያ በትብብር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳህለማርያም ገብረ መድህን በበኩላቸው፤ የኦሮሚያ ክልል እንደሀገር ለሻይ ቅጠል ልማት ምቹ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተለይ በጅማ፣ ቡኖ በደሌ እና ኢሉአባቦራ ዞኖች ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡በተበታተነ መልኩ ይካሄድ የነበረውን የሻይ ቅጠል ተከላ ሥራ ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ በክላስተር ደረጃ ማምረት ተጀምሯል ብለዋል፡፡
በዚህም 2016 በጀት ዓመት ብቻ ከሰባት ሺህ 813 ሄክታር በላይ መሬት በሻይ ቅጠል ችግኝ እንደተሸፈነ ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ከ48 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተከላ ተካሂዷል፡፡ በተያዘው ዓመት ለሚደረገው ተከላም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
እስካሁን ለተገኘው ውጤት እና አሁንም እየተሠሩ ላሉ ሥራዎች የክልሉ ግብርና ቢሮ እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች መላውን ህብረተሰብ ከባለሙያዎች እንዲሁም አርሶ አደሮችን በማስተባበር ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሻይ ምርት ምቹ የሆነ የአየር ጸባይና የአፈር ሁኔታ እንዳላት አስታውሰው፤ ምርቱ በሚፈለገው ደረጃ ባለመስፋፋቱ እስካሁን እንደ ሀገር ከሻይ ቅጠል የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በዓመት ከሶስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የበለጠ አልነበረም ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን ይህን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች በመንግሥት በኩል ተቀምጦ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በዘርፉ ለሚሳተፉ ባለሀብቶችም የተለያየ ማበረታቻ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የሻይ ቅጠል ምርት አንድ ጊዜ ከተተከለ ለ30 እና 40 ዓመታት ምርቱ የሚቆይ፣ በየ15 ቀኑ ምርቱን በመቅጠፍ ገቢ ማግኘት የሚያስችል ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ከዚህ አኳያም ከኦሮሚያ ባለፈ ሌሎች ክልሎችም የሻይ ምርትን ለማስፋት በትኩረት ሊሠሩበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም