አዲስ አበባ፡- ጨረታ የወጣባቸው ሦስት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እና ስምንት የጥናትና ዲዛይን ጨረታዎች እንዲቋረጡ መደረጉን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ::
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የምክር ቤት አባላት ላነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ ጨረታ የወጣባቸው ሦስት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እና ስምንት የጥናትና ዲዛይን ጨረታዎች እንዲቋረጡ መደረጉን ተናግረዋል::
ጨረታዎቹ እንዲቋረጡ የተደረገው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስጠንቶ ሥራ ላይ ለማዋል ያሰበውን አዲስ አሠራር ተከትለው እንዲተገበሩ ለማስቻል እንደሆነም ጠቅሰዋል:: ፕሮጀክቶችን መቁጠር ብቻ ሳይሆን ወደ ውጤት መቀየር ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የተዘጋጀውን አዲስ ደረጃ (ስታንዳርድ) መከተል ያስፈልጋል ብለዋል::
ከአሁን በፊት የግንባታ ሥራዎች የሚመረጡበት፣ ውሳኔ የሚያገኙበትና ወደ ግንባታ የሚገቡበት መንገድ ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ አለመኖር፣ የአዋጭነት ጥናትና የተሟላ ዲዛይን ሥራ ያልተሠራላቸው መሆን፣ የተቋራጮች የአቅም ውሱንነት ፣ የበጀት እጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር ፣ ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለፕሮጀክቶች መዘግየት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብለው የተለዩ ስለመሆናቸውም አብራርተዋል:: ለዚህ ሁሉ ችግር መፈጠር ስታንዳርድን የጠበቀ የአሠራር ሥርዓት አለመኖር እንደሆነ ተናግረዋል::
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሀብት የፈሰሰባቸውና 120 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተው፤ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች የቅድመ አዋጭነት ጥናት ሳይጠናላቸውና ዲዛይናቸው ሳያልቅ ሥራቸው የተጀመረ በመሆኑ በወቅቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ብለዋል:: ሥራቸውን ከ50 በመቶ በላይ ያልገፉት አንዳንዶቹም የዲዛይን ክለሳ ተደርጎላቸው እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል::
ፕሮጀክቶች ስታንዳርድን ያልተከተሉ በመሆናቸው ለጊዜ ብክነት፣ ለተጨማሪ ወጪና ለሥራ ጥራት ጉድለት እንደተዳረጉም ጠቅሰዋል:: ፕሮጀክቶች እንደማይጠናቀቁ እየታወቀ፤ የሕዝብን ሀብት እየበተኑና ቁጥር እየጠቀሱ አሉን እያሉ መዘርዘር ከዚህ በኋላ አይኖርም ነው ያሉት::
ለረዥም ጊዜ ሀብት እየፈሰሰባቸውና ሕዝብ እያለቀሰባቸው ያሉ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለሕዝቡ ተስፋ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ አዲስ ፕሮጀክት ከመሥራትና አዲስ ሀብት ከማፍሰስ በፊት እስከ አሁን የፈሰሰውን ሀብት ወደ ውጤት ለመቀየር በትኩረት ይሠራል ብለዋል::
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከደረጃዎች ኢንስቲትዩትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር ካዘጋጀው ስታንዳርድ በተጨማሪ በራሱ በኩል ያለውን ክፍተትም ተመልክቷል ነው ያሉት:: በመሆኑም ከአሁን በፊት በተቋሙ የሌለ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኦፊስ በመክፈት እያንዳንዱን ፕሮጀክት በቦታው ሆኖ የመከታተል ሥራ ይሠራል ብለዋል:: ከዚህ በኋላ ተቋራጮች ሥራቸውን የሚሠሩት የፕሮጀክቱ ባለቤቶች ባሉበት ቦታ እንደሚሆንም አስምረውበታል::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም