አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ በበርካታ የኢኮኖሚ መስኮች እየታየ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ በበርካታ የኢኮኖሚ መስኮች እየታየ ነው። በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ቡናን በዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂ በማልማት እና በማሽን በመልቀም ምርታማነትን በሄክታር 60 ኩንታል ማድረስ ተችሏል። ይህን በሁሉም የቡና አምራች አካባቢዎች በማስፋት የዘርፉን የወጪ ንግድ ገቢ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በምዕራብ ጉጂ ገላን ወረዳ ከዚህ ቀደም ታርሶ የማያውቅ መሬት በቀርጫንሼ ትሬዲንግ አማካኝነት ወደ ምርታማ የቡና እርሻ ስፍራነት ተቀይሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀርጫንሼ የለማው መሬት ሜካናይዝድ እርሻን በመጠቀም በሄክታር 60 ኩንታል ምርት የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የቡና ችግኝ ተክለዋል።
በተያያዘ በጉብኝታቸውም በሻኪሶ በቅርቡ የተመረቀው የዋይ ኤም ጂ ጎልድ ማይኒንግ ተቋምና በጉጂ በኢትዮጵያ መሪ የወርቅ ምርት ኩባንያዎች አንዱ የሆነውን የሚድሮክ ጎልድ የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዕድሎች ማሳያ የሆነች በአህጉሩ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልጸው፤ በማደግ ላይ ካሉት ዘርፎቿ መካከል ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ሰፊ አቅም ያለውና እድገቷን በመምራት ትልቅ ስፍራ እየያዘ የመጣው የወርቅ ማምረት ኢንዱስትሪ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በወርቅ ክምችት የታደሉት የሻኪሶ እና ሰፊው የጉጂ አካባቢ የማዕድን ማውጣት ሥራው ዐቢይ ስፍራዎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሻኪሶ በቅርቡ የተመረቀው የዋይ ኤም ጂ ጎልድ ማይኒንግ ተቋም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተስፋ ሰጪ እድሎችን ይዞ የመጣ ሆኗል ነው ያሉት።
በመሬት ስበት ተመሥርቶ የሚሠራውን ዘመናዊ የማዕድን ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው የዋይ ኤም ጂ የምርት ሥራ ጠንቀኛ ኬሚካሎችን ከመጠቀም የተጠበቀ፣ ፈጠራ የሞላበት እና የአካባቢ ጥበቃ ተስማሚነትን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በጉጂ በነበረኝ ጉብኝት በኢትዮጵያ መሪ የወርቅ ምርት ኩባንያዎች አንዱ የሆነውን የሚድሮክ ጎልድ የሥራ እንቅስቃሴንም ተመልክቻለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በዘርፉ ቀዳሚ እንደመሆኑ በትልቅ አቅም እና ደረጃ በሚሠራው የወርቅ ምርት ሥራ ለኢትዮጵያ የማዕድን ከባቢ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የሀዋሳ ኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማትም የራሱ ልዩ አሠራር ያለው ሆኖ በአዲስ አበባ የተጀመረውን የከተማ ልማት ጥረት ያስቀጠለ ሥራ ነው ብለዋል።
ሰፋ ያሉ የእግረኛ መንገዶች፣ የተለያዩ የብስክሌት መንገዶች፣ በሀገር ውስጥ የተመረቱ ስማርት የመብራት ምሰሶዎች ወዘተ የሥራውን ፈጠራ እና ቀጣይነት እንደሚያሳዩ ጠቁመው፤ ይሁንና የከተማ ልማት የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አይደለም፤ የተሳካ ይሆን ዘንድ የማኅበረሰቡን ንቁ ተሳትፎ ይሻል። ርምጃዎቻችን መልካም ቢሆኑም እነዚህን አሻጋሪ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ብዙ ሥራ ይቀረናል። ኢትዮጵያ ሰፊ ሀብት የሞላባት ሀገር እንደመሆኗ እምቅ አቅሟ ግዙፍ ነው። ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህን በመገንዘብ ለሥራ የሚነሱበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም