አዲስ አበባ፡– ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአብሮነት ለመኖር የመሠረቱት አሰባሳቢና አቃፊ ሥርዓት መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በአርባምንጭ ከተማ ትናንት በድምቀት ተከብሯል።
አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዓሉ ላይ እንደገለጹት፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ለማስከበር ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
ምክር ቤቱ በዋናነት እንደ ሀገር የብዝኃነት አያያዝ እንዲጎለብት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት ሥር እንዲሰድ ሲሠራ መቆየቱንና አሁንም እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት 18 ዓመታት በዓሉ በተከታታይ መከበሩ በሀገራዊ አንድነት ግንባታ ላይ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት አስተዋፅዖ የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ በተጨማሪም በሕገ-መንግሥት ላይ የነበረ የግንዛቤ ክፍተትን ለመሙላት በዓሉ የአስተምሕሮ መድረክ ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዓሉ ሁሉም የሀገሪቷ ሕዝቦች ማንነታቸው እንዲከበር እንዲሁም ለፍትሕና ለነፃነት መረጋገጥ በጋራ እንዲሠሩ አድርጓል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ይህ ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአብሮነት ለመኖር የመሠረቱት አሰባሳቢ፣ አቃፊና አሳታፊ ሥርዓት መሆኑንም ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በዓሉ መከበሩ በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት ያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተከበሩ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓላት የሕዝቡን አብሮነት ለማጽናት ማስቻላቸውን አፈ ጉባዔ አገኘሁ አስረድተዋል።
በመንግሥት ደረጃም ከልዩነት ይልቅ አብሮነት ለማጽናት፣ ከመራራቅ ይልቅ ለመቀራረብ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውሰዋል። በዓሉ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲሁም ለሕገ መንግሥት አስተምሕሮ መሠረት የጣለ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የፍቅር ምንጭና የአንድነት መሠረት መሆን ችሏል። የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን ተስፋ በሚያስቆረጥ መልኩ በድምቀት ተከብሯል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ውበትና ፀጋ የሚታደሉት እንጂ የሚታገሉት አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ብልፅግና ፈተናዎችን አልፎ ተስፋ ያላትና አስተማማኝ ሀገር እንድትሆን አስችሏል ነው ያሉት።
ሀገራዊ ለውጡ ከይስሙላ ፌዴራሊዝም ወደ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ያሸጋገረ እንዲሁም ነጠላ ትርክትን ወደ ብሔራዊ ትርክት በመቀየር ቱሩፋት እንዳስገኘ ገልጸው፤ ለዚህ ክልሉ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ማጎልበት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ነው የተናገሩት።
በዓሉ “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በደማቅ ሁኔታ መከበሩን ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም