አዲስ አበባ፡- አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ በአግባቡ መተግበር የገጠር መዋቅራዊ ሽግግርን በፍጥነት እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ሀገሪቱ ተግባራዊ እያደረገች ለምትገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ (ሪፎርም) ውጤታማነት መሠረት የሚጥል እንደሆነም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ዳይሬክተር ታደለ ማሞ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ በተሟላ መንገድ መተግበሩ በገጠር ሁለንተናዊ እና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ (ሪፎርም) ውጤታማነት ፖሊሲው መሠረት የሚጥል ነው።
በዋናነትም ፖሊሲው ከሀገሪቱ ሕዝብ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው አርሶ አደር የግብርና ሥርዓት በማዘመን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ብሎም ለኢንዱስትሪው ሁነኛ መጋቢ ሆኖ እንዲቀጥል፤ ሰፊው የሰው ኃይል በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ ሰንቆ የተቀረፀ መሆኑን ታደለ (ዶ/ር) አመልክተዋል። ለዚህም ደግሞ በዝናብና በበሬ ላይ የተንጠለጠለውን የአመራረት ሂደት ወደ መስኖና መካናይዜሽን እርሻ በመቀየር፤ በምርምርና በቴክኖሎጂ በመደገፍ በጥቂት አርሶ አደሮች ብቻ በማምረት የገጠሩ ክፍል መዋቅራዊ ሽግግር በወሳኝነት ማሳለጥ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ግብርና መዋቅራዊ ሽግግር በሚመጣበት ወቅት አምስት በመቶ ብቻ የሚሆነው አርሶ አደር ቀሪውን 95 በመቶ የሚሆነውንና በከተማ የሚኖረውን ሕዝብ እንደሚመግቡ፤ የማምረት ሂደቱም በቴክኖሎጂ እየተመራ ኢንዱስትሪውን ይደግፋል። ኢንዱስትሪውም ለግብርናው ዘርፍ ግብዓት እንደሚያቀርብ ታሳቢ ተደርጎ ነው የተነደፈው። የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲያድግ ግብርናን ያንቀሳቅሰዋል፤ የፊትዮሽና የኋልዮሽ ግንኙነታቸውንም ያስፋፋል። ከዚህ አኳያም የግብርና ገጠር ትራንስፎርሜሽን እንዲመጣ ሌሎቹም በተመጣጣኝ መልኩ ማደግ አለባቸው።
‹‹ግብርና ብቻውን የቱንም ያህል ቢያድግ ኢንዱስትሪውና አገልግሎት ዘርፉ ካላደገ ትርጉም የለውም›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሲያድግም እንደማዳበሪያ፣ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚስፋፉበት ዕድል ስለሚፈጠር አርሶ አደሩ በቀላሉ ግብዓት ተጠቅመው ምርታቸውን ለማሳደግ እንደሚያስችላቸው አስገንዝበዋል።
የምርምር ተቋማት ምርት የሚያሳድጉ አዳዲስ ምርምሮችን በማፍለቅ፤ ግብርና ኤክስቴንሽኑ አርሶ አደሩን በመደገፍ፤ የአገልግሎት ዘርፉ መጠናከር እንዲሁም እንደ መብራት፤ መንገድና ውሃ ያሉ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በተሟላ መልኩ ማከናወን የሚጠበቅባቸው መሆኑን አብራርተዋል።
‹‹ፖሊሲው ያስቀመጠው አቅጣጫ ብቻ ነው፤ በተጨባጭ በገጠር መዋቅራዊ ሽግግር እንዲመጣ ግን ግልፅ የሆኑ የማስፈፃሚያ ስልቶችና መመሪያዎች በተዋረድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል›› የሚሉት ታደለ (ዶ/ር)፤ ለዚህም በፖሊሲው ዋነኛ ዓላማ ዙሪያ ከከፍተኛ እስከ ታችኛው ያለ መንግሥታዊ መዋቅር ላይ እንዲሁም ለዘርፉ ተዋናዮች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተጨማሪም ፖሊሲውን በተጨባጭ መሬት ላይ ለማውረድም ሆነ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሀገርን ሠላም የማስጠበቁ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም