ኢትዮጵያ ከዓለም ኃያላን ሀገራት ጋር ያደረገችው የጦርነትም ሆነ የዲፕሎማሲ ድል ለዛሬው ትውልድ ወኔ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ከኃያላን ሀገራት ጋር በጦርነትም ሆነ በዲፕሎማሲ ተዋግታ እና ተከራክራ ያገኘቻቸውን ድሎች የምናስታውሰው፡፡ ከእነዚህ ድሎች አንዱ የዓድዋው ጥንስስ የሆነው የአምባላጌው ጦርነት ነው። ጣሊያን በአምባላጌው ጦርነት ሲሸነፍ፤ ተጠራርጎ መውጣት ሲገባው አሻፈረኝ ብሎ ቀጠለበት፤ በዓድዋው ጦርነት ዓለም አቀፍ ውርደትን ተከናንቦ ወጣ፡፡ በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ129 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም የተከሰተውን የአምባላጌ ጦርነት እናስታውሳለን፡፡
ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው በዚህ ሳምንት ውስጥ የነበሩ ሌሎች ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ የታሪክ ክስተቶችን እናስታውስ፡፡
ከ51 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 24 ቀን 1966 ዓ.ም አንጋፋው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሥራ ጀመረ፡፡ አሁን ላይ ብዙ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለረጅም ዓመታት ሪፈራል ሆስፒታል ሆኖ ከመላ ሀገሪቱ የሚመጡ ዜጎችን ሲያገለግል ቆይቷል። ሙሉ ታሪኩን ከሦስት ዓመታት በፊት በዚሁ ዓምድ አስታውሰን እንደነበር ልብ ይሏል፡፡
ከ457 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 25 ቀን 1560 ዓ.ም የአጼ ልብነ ድንግል ባለቤት የነበሩትና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ከያዙ እንስቶች መካከል ተጠቃሽ የሆኑት እቴጌ ሰብለወንጌል አረፉ፡፡
ከ90 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር እንደሰበብ የተጠቀመችበት ታሪካዊው የወልወል ግጭት ተከሰተ፡፡ ኢጣሊያ የዓድዋን ቂም ለመወጣት ዝግጅት ካጠናቀቀች በኋላ ኢትዮጵያን የምትወርበትን አጋጣሚ መጠባበቅ ጀመረች፡፡ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም የኢጣሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ሱማሌላንድ መካከል ያለውን ወሰን ለመከለል የተላኩትን ሰዎች ይጠብቁ በነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈቱባቸው፡፡ (ኢጣሊያ በአካባቢው ያለው የኢጣሊያ ሱማሌላንድ ግዛቷ ስለሆነ ወታደሮቿ በአካባቢው ነበሩ) ውጊያ ተደረገና በሁለቱም ወገኖች በኩል ሰውነት ቆሰለ፤ አካል ጎደለ፣ የሰው ሕይወት ጠፋ፡፡
የወልወል ግጭት በታሪክ ኢጣሊያ ለብዙ ዘመናት ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የቆየችውን ኢትዮጵያን ለመውረር የነደፈችውን ዕቅዷን ለማሳካት እንደሽፋን የተጠቀመችበት ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
ከ21 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም የቤተ ክህነት ሊቅ፣ ደራሲ፣ አርበኛ፣ መምህር እና ዲፕሎማት የነበሩት የክብር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ አረፉ፡፡ ሀዲስ አለማየሁ በተለይም በፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፋቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ፡፡
ከ52 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን ኅዳር 29 ቀን 1965 ዓ.ም የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝና የ60ዎቹ ትውልድ ንቅናቄ ዋና ተዋናይ የነበረው ዋለልኝ መኮንን ተገደለ፡፡ የተገደለው ከአውሮፕላን ጠለፋ ሙከራ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የጸደቀው እና ቀኑ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ተብሎ እንዲከበር የተደረገው ዋለልኝ መኮንንን ለማስታወስ ነው የሚሉ አስተያየቶችም አሉ፡፡
ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት የኖቤል ሽልማት ነው፡፡ ከአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጋር ያለን ልዩነት ጳጉሜ 6 በምትሆን ዓመት ከፍ ዝቅ ይላል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ በኅዳር ወር መጨረሻ ይታወሳል፡፡
የኖቤል ሽልማት መስጠት የተጀመረው በዚህ ሳምንት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ዴሴምበር 10 ቀን 1901 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1894 ዓ.ም) ነው፡፡ 123 ዓመት ሆነው ማለት ነው፡፡
ሽልማቱ የተጀመረው የአልፍሬድ ኖቤል አምስተኛው ሙት ዓመት በተዘከረበት ነው። የመጀመሪያዎቹ ሽልማቶችም የተሰጡት በስዊድን ስቶክሆልም ሲሆን፣ ሽልማቶቹ የተሰጡባቸው መስኮችም ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ህክምና፣ ሥነ ጽሁፍ እና ሰላም ናቸው።
ቆይቶም ምጣኔ ሀብት ተጨምሮበታል። ኖቤል በ1895 ባረቀቀው መመሪያ መሠረት ሽልማቱ እየተሰጠ ይገኛል። በስዊድናዊው አልፍሬድ ኖቤል ስም የተዘጋጀው ይህ ሽልማት ለሰው ልጅ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ተግባሮች ላከናወኑ እንዲሰጥ በሚል ኖቤል በተናዘዘው መሠረት የሚሰጥ ነው። ተሸላሚው የወርቅ ሜዳሊያ፣ ዲፕሎማ እና የገንዘብ ሽልማት ይሰጠዋል። ሎሬት በመባልም እንዲጠራ ይደረጋል።
ጥቁር አሜሪካዊው የሠብዓዊ መብት ዋና ተሟጋችና ሰማዕት ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ የኖቤል ሰላም ሽልማት ከተቀበሉት መካከል ይገኙበታል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኽም ቤጊን እና የግብጽ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት የኖቤል የሰላም ሽልማት ተካፋዮች ሽልማቱን ተቀብለዋል። የፍልስጤም መሪ ያሲር አራፋት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሐቅ ራቢን እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሺሞን ፔሬዝ በጋራ የተሰጣቸውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተቀበሉት መካከል ይገኙበታል።
የናይጄሪያው ወሌ ሶይንካ፣ የግብፁ ናጂብ ማህፉዝ እና የደቡብ አፍሪካው ናዲን ጎርዲመር በሥነ ጽሑፍ ሽልማትን ተቀብለዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ከአምስት ዓመት በፊት የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ሽልማት የበቁት ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በሀገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መውሰድ በጀመሯቸው ርምጃዎችና በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር የኖቤል ሰላም ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው።
አሁን በዝርዝር ወደምናየው አምባ አላጌው ጦርነት እንመለስ፡፡
የአምባ አላጌ ጦርነት የተካሄደው ከዓድዋ ጦርነት ሦስት ወራት ቀደም ብሎ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር። የዓድዋ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
የአምባላጌውን ውጊያ የጀመሩት ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራ) እና ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባ ነጋ) ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የበላይ አዛዥ ደግሞ ልዑል ራስ መኮንን ነበሩ፡፡
ጦርነቱም በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን የወራሪው የኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ መሸነፉ በመላው አውሮፓ በተለይም በተሸናፊዋ ኢጣሊያ ምድር ከፍተኛ ፍርሃት፣ ብስጭትና ቁጣ ፈጥሮ ነበር፡፡
በጦርነቱ ዕለት ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለዓድዋ ጦርነት ዘመቻ ከአዲስ አበባ ተነስተው እየተጓዙና በመንገዳቸውም ላይ ሕዝቡን እያነጋገሩ ገና ወሎ ውስጥ ነበሩ፡፡ የድሉን ዜና ለዳግማዊ ምኒልክ የላኩላቸው ራስ መንገሻ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጣሊያንን አላጌ (አንዳንዶች አላጄ እያሉም ይጠሩታል) በር ላይ ድል መቱ፤ ወራሪው የጣልያን ጦር ለዓመታት ሲቋምጥባት የኖረችውን ኢትዮጵያ በወረረበት ወቅት በሰሜን በኩል ያለውን የኢትዮጵያ ክፍል በቅኝ ግዛቱ ውስጥ እያደረገ ወደታች በመግፋት እስከ አሸንጌ ሀይቅ ድረስ ግዛቱን አሰፋ።
ይህንንም ወረራ ለመመከት ሕዝባቸው አንድ ሆኖ እንዲሰለፍ ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ በነበሩት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አማካኝነት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሁሉም አቅጣጫ በጀግኖች የጦር አበጋዞቹ እየተመራ ጉዞውን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አደረገ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ይህንን ወራሪ የጣሊያን ጦር ለመመከት ይቻለው ዘንድ ከመቀሌ በስተ ደቡብ 80 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚገኘው የአምባ አላጌ (አምባ አላጄ) ተራራ ላይ መሽጎ የሠራዊቱን መንገድ ዘጋ።
በራስ መኮንን የሚመራው ቀዳሚ ጦር ቦታውን ለማስለቀቅ ከፍተኛ የሆነ የድርድር ሥራ ቢከውንም በማጆር ቶዜሊ የሚመራው የጣሊያን ኃይል ቦታውን ‹‹አለቅም!›› በማለት አሻፈረኝ አለ። በኢትዮጵያ ወገን ከነበሩ የጦር መሪዎች መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ እና ቀኝ አዝማች ታፈሰ ከመሪዎቻቸው ፈቃድ ሳያገኙ ጦርነቱን በንዴት አስጀመሩ። በተጀመረው ድንገተኛ ውጊያ የጣሊያን ጦር ቀድሞ ባዘጋጀው ምሽግ ተደላድሎ ከፍተኛ ጥቃት ቢፈፅምም፤ ሁሉም የጦር መኳንንት በድንገት ያለፈቃድ የተጀመረውን ጦርነት ተቀላቀሉ።
ጀግናው ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባ ነጋ) ጠላት የዘጋውን መንገድ ትተው በሌላ መንገድ ከኋላው ዞረው የአላጌን ተራራ አናት ተቆጣጥረው ቁልቁል እየተኮሱ ጠላትን ይፈጁት ጀመር። ከፊት ራስ መኮንን፤ ራስ ወሌ፤ ራስ መንገሻ እና ራስ ሚካኤል (በኋላ ንጉሥ) ሠራዊቱን አንቀሳቅሰው የማጆር ቶዜሊን ጦር ክፉኛ ጎዱት። በፊታውራሪ ገበየሁ አማካኝነት ያለ ፍቃድ የተጀመረው ጦርነት በጀገኖች ኢትዮጵያውያን ፍርክስክሱ ሲወጣ የጦሩ መሪ ማጆር ቶዜሊ በቦታው ላይ ፊታውራሪ አባ ወርጂ በተባሉ ጀግና አጥፍቶ ጠፊነት ሕይወቱን አጥቷል።
ጦርነቱ አንገብጋቢና አስቸኳይ ስለነበር ያለፈቃድ የተጀመረ ቢሆንም ድል ለኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች ሆነ። ከውጊያው የተረፈው የጠላት ጦር እግሬ አውጪኝ ብሎ በመፈርጠጥ የመቀሌው እንዳየሱስ ምሽግ ውስጥ ሰፈረ። ለጀግኖቹ ለእነ ፊታውራሪ ገበየሁ እንዲህ ተብሎ ነበር፡፡
የንጉሥ ፊታውራሪ የጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
ለምሳም አልበቁት ቁርስ አደረጋቸው!
የአምባ አላጌው ጦርነት ላይ ከፊታውራሪ ገበየሁ ሌላ ትልቅ ጀብዱ የፈፀሙት ጀግና ፊታውራሪ አባ ውርጂ ነበሩ። እርሳቸው በጦርነቱ ላይ ማጆር ቶዜሊን ብቻውን አገኙት። ጦሩን ከፍ ብሎ እየቃኘ እያለ ድንገት ተያዩ፤ እርሱ ሽጉጡን እስኪያወጣ እንኳን ዕድል ሳይሰጡት፣ ዘለው ትግል ገጠሙት፣ በዚህ ትግል ተያይዘው ወደ ገደል ጫፍ አደረሱና ሲወረውሩት እርሱም የሞት ሞቱን እርሳቸውን እንቅ አድርጎ ይዟቸው ስለነበር፤ አብረው ተያይዘው ከገደሉ ወደቁ። በዚህን ጊዜ የወቅቱ አዝማሪ እንዲህ አለ፡፡
ጄኔራሉን ማጆር ቶዚሊ
ማን ይነካው ነበር ያለ ፈጣሪ
ገደል ሰደደው አንድ ፊት አውራሪ!
በዚህ ሁኔታ ተጀምሮ የነበረው የጣሊያን እና የኢትዮጵያ ጦርነት፤ ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ‹‹ምታ ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት›› ብሎ የሀገሪቱ ቆራጥ ጀግኖች በመነሳታቸው የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በታላቁ የዓድዋ ድል ፍጻሜውን አገኘ፡፡
በዚሁ እግረ መንገድ ስለ ራስ አሉላ አባ ነጋ ጥቂት እንበል፡፡
የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጀኔራል በመባልም ይገለጻሉ፡፡ በፈረስ ስማቸው ራስ ‹‹አሉላ አባ ነጋ›› በመዝገብ ስማቸው ደግሞ አሉላ እንግዳ ቁቢን ይባላሉ። አሉላ አባ ነጋን የጦር መሪ፣ ሀገር አቅኚ፣ ዲፕሎማት፣ የደህንነት ሰው፣ አርቆ አሳቢ ጀግና የሚሉት ቅጽሎች ብቻ አይገልጿቸውም ይባላል፡፡ ከኩፊት ጀምሮ እስከ ዓድዋ ድረስ ነበልባል ክንዳቸውን የቀመሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች የእርሳቸውን ማንነት ይመሰክራሉ፡፡
ራስ አሉላ የተወለዱት በተምቤን ሲሆን አባታቸው እንግዳ ቁቢ ይባላሉ። ራስ አሉላ አመራርን በተፈጥሮ የተቸሩ መሆናቸውን እስራኤላዊው የታሪክ ጸሐፊ ሀጋይ ኤርሊችን ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሠራው ፕሮግራም እንደተገለጸው፤ ራስ አሉላ በልጅነታቸው ልጆችን እንደ ወታደር ሰብስበው እየመሩ ወደ ሰርግ ቤት የሚሄዱ ሰዎችን አስቁመው ወደ የት እንደሚሄዱ ይጠይቋቸው ነበር፡፡ ሰዎችም ‹‹ወዲ ቁቢ ‘ቤተመንግሥቴ ነው›› ብለው በሠፈሩበት የእቃ እቃ ጨዋታ ቦታ እየሄዱ ‹‹ራስ አሉላ›› በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸው ነበር።
አሉላ የእንደርታ ባላባት ለነበሩት ራስ አርዓያ ድምጹ አገልጋይ በመሆን ውትድርናን እንደተማሩ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ ብዙም ሳይቆዩ የደጃዝማች ካሳ ምርጫ (የወደፊቱ አፄ ዮሐንስ አራተኛ) አጎት የሆኑትን ራስ አርዓያን ትኩረት መያዝ ቻሉ፡፡ ራስ አርዓያም የአሉላን ታታሪነት እና ታማኝነት በማየት የእልፍኝ አስከልካያቸው አደረጓቸው። ኤርሊች እንደጻፉት አፄ ዮሐንስ ከተቀናቃኛቸው ንጉሥ ተክለጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጦርነት ወጣቱ አሉላ ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን በመማረክ የመጀመሪያ የጦር ሜዳ ጀብዷቸውን አስመዘገቡ፡፡ አሉላ በወቅቱ አባባል ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከነበረው (ጭሰኛ) ቤተሰብ ቢወጡም በታማኝነታቸው እና በጀግንነታቸው የመሳፍንት እና የነገሥታት ዘሮች ብቻ በሚያገኙት ከፍተኛ የሥልጣን ተዋረድ መሰላል ላይ በፍጥነት ሊወጡ ችለዋል።
ራስ አሉላ፤ በኩፊት፣ በዶጋሊ፣ በገላባት፣ በአምባላጌ፣ በዓድዋ… የኢትዮጵያን ክብር ያስጠበቁ ጀግና የጦር መሪ ናቸው፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም