ሴቶች በኢነርጂው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ሴቶች በኢነርጂው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ሲል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሴቶች በኢነርጂ ማህበር፤ በኢነርጂ ዘርፍ ስኬት ላስመዘገቡ ሴቶች የእውቅና መርሃ-ግብር ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ሴቶች በኢነርጂው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ እድገትን እውን ለማድረግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

ሴቶች በኢነርጂው ዘርፉ እንዲሳተፉ ማበረታታት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማሳለጥና ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ስለሚጠቅም ወደ አመራርነት የማምጣትና ተሳትፏቸውን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

እየተሰራ ባለው የኢነርጂ ተደራሽነት አብዛኛውን ጊዜ ተጠቃሚ የሚሆኑት እናቶችና ሕፃናት ናቸው፤ እናቶች በኢነርጂ ዘርፍ ያላቸውን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በዘርፉ ተሳትፏቸውን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢነርጂ የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤ የእናቶች ጤንነትን ለመጠበቅ ንፁህ ምድጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢነርጂ ለማንኛውም ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆነ ግብዓት ነው፤ ኢትዮጵያ ያላትን የኢነርጂ አቅም በመጠቀም ሁለተናዊ እድገት ለማምጣት እየሰራች መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች የኢነርጂ ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አደይ ጌታቸው በበኩላቸው፤በኢነርጂው ዘርፍ ሴቶች ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ የእኩልነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታዊ ሀገር ልማት ወሳኝ ነው፡፡

በዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ማበረታታትና ባላቸው አቅም ላይ ኢንቨስት ማድረግ ኢኮኖሚያዊ እድገትን እውን ለማድረግ ይጠቅማል ነው ያሉት፡፡

በአፍሪካ አህጉር በኢነርጂ ዘርፍ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ ከወንዶች አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው ያሉት ወይዘሮ አደይ፤ ምክንያቱም ሴቶች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉ በመሆኑ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ዘርፉ ለሴቶች ከባድ ተደርጎ በማህበረሰቡ ዘንድ በመታሰቡ፤ ታዳጊ ሴቶች ሙያውን በአግባቡ እንዳያውቁት በርካት ተግዳሮቶች መኖራቸው የሴቶችን ተሳትፎ በዘርፉ ላይ አናሳ አድርጎታል ሲሉም ገልጸዋል።

ማህበሩ ያለውን ተግዳሮት በመረዳት ለጠንካራና ለታታሪ ሴቶች ትኩረት የመስጠት ፤ በተለይም ታዳጊ ሴቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ እውቅና በመስጠትና ታሪክን የመቀየር ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የኢትጵያ ሴቶች በኢነርጂ ማህበር፤ ሴቶች በኢነርጂ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ላለፉት አራት ዓመታት እየሰራ ነው፤ እየሰራ ያለውን ስራም አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ወይዘሮ አደይ ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ህዳር 28/2017 ዓ.ም

Recommended For You