በዓሉ ብዝኃነትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበት ነው

አዲስ አበባ፡- የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበት መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለህብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል አክብሯል፡፡

በወቅቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት፤ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ታዳሚዎች እሴቶቻቸውን፣ባህሎቻቸውንና ልምዶቻቸውን በመለዋወጥ ብዝኃነትን እና ኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናክሩበትና ስለ ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚወያዩበት የኢትዮጵያውያን ቀን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነት ካላቸው የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አመልክተው፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዝኃነትን በአግባቡ ከማስተናገድ እና ኅብረብሔራዊ አንድነት ከማጠናከር አንጻር ጉድለቶች መታየታቸውን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና አንድነትን ለማጠናከር ውይይትና ምክክር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ልዩነትን ማጥበብ እና የጋራ ሃሳብ በማፍለቅ ህብረብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቋንቋ፣ ባህልና አመለካከት ያለባት ሁሉም በህብር የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን አንስተው፤ የተሰሩ የልማት ስራዎችም ከተማዋን አዲስ ገጽታ ያጎናጸፉና ሀገሪቱን የዕድገት ማሳያ እያደረጋት ይገኛል ብለዋል።

ኅብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ፣ ዘላቂ ሰላምን በሚያሰፍኑ ጉዳዮች ላይ የተጀመረው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የመሠረተ ልማት እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔረሰቦች፣ቋንቋዎች፣ባህሎች፣ ትውፊቶችና ወጎች ያሉባት ድንቅ ሀገር መሆኗን አንስተው፤ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ብዝኃነትን መገንባት ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት ከብሔር ብሔረሰቦች መብት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢ ግጭቶች መከሰታቸውን አስታውሰው፤ የብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ጠንካራ መተሳሰብና አብሮነት ያሉባት ሀገር ለመገንባት የራሱን ድርሻ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያውያን ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ይበዛሉ፡፡ ያሉንን ልዩነቶች እንደ ጌጥና ጉልበት መጠቀም ይኖርብናል ያሉት ከንቲባዋ፤ አንድነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ በመጣል ለቀጣይ ትውልድ ሀገረ ግንባታ ስንቅ ማስተላለፍ ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ለኅብረ ብሔራዊነት ማሳያ የሆነች ትልቋ የኢትዮጵያውያን ቤት እንደሆነች ገልጸው፤ ለአንድነት ሳንካ የሆኑትን ለይተን በማስወገድ እና አካታችነትን በመከተል አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ምቹ እንድትሆን የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ህዳር 28/2017 ዓ.ም

Recommended For You