በባህር ዳር ከተማ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ኮሪደር ልማት ለማካሄድ ታቅዶ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– በባህር ዳር ከተማ 22 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ለመስራት ታቅዶ ከዚህ ውስጥ ሶስት ኪሎ ሜትሩን ለማጠናቀቅ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማዋ 22 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ለማከናወን ታቅዶ አሁን ላይ ሶስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ስራ ተጀምሮ እየተፋጠነ ነው፡፡

የሶስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራው ከተጀመረ ሁለት ወራት ማስቆጠሩን አስታውሰው፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአጭር ጊዜያት ለማጠናቀቅ ሰፊ ክትትል እየተደረገ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

በዋናነትም የኮሪደር ልማቱ ወደ ሶስት ሜትር የሚሆን ስፋት ያለው የሳይክል መንገድ በሁለቱም አቅጣጫ እንደሚኖረው፣ ከአምስት እስከ ስምንት ሜትር ስፋት የሚደርስ የእግረኛ መንገድ፣ ከሶስት እስከ አራት ነጥብ አምስት የሚሆን አረንጓዴ ቦታ፣ የሳይክልና የባስ ማቆሚያዎች ፣ አልፎ አልፎ የፈጣን ምግብ መስተንግዶ አገልግሎት መስጫዎች፣ የሕዝብ መዝናኛዎች እንዲሁም ፋውንቴኖች እንደሚኖሩትም ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም የመብራት፣ ውሃና የቴሌኮም አገልግሎት መስጫዎች መስመሮች አሁን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ታሳቢ ያደረገ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር ኮሪደር ልማቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ የሶስት ኪሎ ሜትር ስራ ብቻ እንኳ ከ750 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የአካባቢውን ማህበረሰብ የስራ ባህል ከማዳበር አንፃርም አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመው፤ ቀን ብቻ ሳይሆን ምሽቱን ጨምሮ በሶስት ፈረቃ 18 ሰአት እየተሰራ እንዳለ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ለባለሀብቶች በጨረታ የሚተላለፉ የቢዝነስ ቦታዎች እንደተፈጠሩ ገልፀው፤ይህም ከተማውን ከማልማት አኳያ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ጎን ለጎንም የአጥር ዲዛይን፣ የህንፃዎች ቀለም፣ የህንፃዎች መብራት እንዲሁም የመንገድ መብራት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አብዛኞቹ ህንፃዎችና ቤቶች ከመንገድ ዳር ርቀታቸውን ጠብቀው ከመሰራታቸው አኳያም አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ በልማቱ ምክንያት ከአካባቢው የሚነሳ ሰው እንደሌለም ጠቅሰዋል፡፡

ከካሳም አኳያ የጥቂት ሰዎች የአጥር ክፍያ እንደሚኖርባቸው ገልፀው፤ ከዛ ባሻገር ማህበረሰቡ አጥሩን እንዴት ልጠር፣ ደጄን እንዴት ላሳምር በሚል እያገዛቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ባህር ዳር ከተማ ከዚህ በፊት ውብ እንደሆነች ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁን ደሞ በኮሪደር ልማቱ የማፈራረስና የመቆፋፈር ስራው የበለጠ ለማስዋብና መንገዶቿን ለማስፋፋት ነውና የኮሪደር ልማቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ስራ ለማከናወን መታቀዱን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤ ቀሪዎቹ ኪሎ ሜትሮችም የገንዘብ አቅማቸው እየታየ እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ህዳር 28/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You