አዲስ አበባ፦ ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበብና ባህል ፌስቲቫል በሀገራቱ መካከል አንድነትንና ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ፌስቲቫሉ “ጥበብና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር” በሚል መሪ ቃል ከጥር 15 እስከ 18 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ተገልጿል። የፌስቲቫሉን ዝግጅት አስመልክቶ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከምሥራቅ አፍሪካ ባሕል ፌስቲቫል ተሳታፊዎች ጋር ተወያይቷል። በወቅቱ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሥራ አመራር ሥራ አስፈፃሚ አህመድ መሃመድ እንደገለጹት፤ በፌስቲቫሉ ባህላዊ ክዋኔዎችን፣ ፊልምና ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት ነው።
ምሥራቅ አፍሪካ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ያለበት አካባቢ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቀጣናው በተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች ምክንያት ግጭቶችና መለያየት እንዲሁም ኋላ ቀርነት ያለበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እነዚህን ሕዝቦች የሚያግባቡና ትስስራቸውን የሚያጠናክሩ የባህልና የኪነ ጥበብ ሥራዎች በፌስቲቫሉ እንደሚቀርቡ ጠቁመው፤ የፌስቲቫሉ ዓላማም የቀጣናውን ሕዝቦች ማቀራረብ፣ ማስተዋወቅና የባህል ልውውጥ እንዲኖር ምቹ ዕድል መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፌስቲቫሉ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል አንድነትንና ትብብርን በሚያጠናክር መልኩ ይከናወናል ብለዋል።
ሥራ አስፈፃሚው ፤ ከሦስት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጀው አንደኛው የምሥራቅ አፍሪካ የባሕልና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል የሀገራቱን ትስስርና የባሕል ትውውቅ ያጎለበተ ነበር። ፌስቲቫሉ በተከታታይ መዘጋጀቱ እየጎለበተ የመጣውን አንድነትን ለማጠናከር አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የፌስቲቫሉ ተሳታፊና አዘጋጅ መሆኗ ያላትን የባሕል ጥልቀት አጉልታ ለማውጣት መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑም ተናግረው፤ በባሕል እና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግም እንደሚረዳ አንስተዋል።
ከቀጣናው ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲን እንደገለጹት፤ ፌስቲቫሉ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን ትስስር ለማጠናከር ያለመ ነው።
ፌስቲቫሉን ኢትዮጵያ ማስተናገዷ የሀገሪቱን ባህል አጉልቶ ለማሳየት እንደሚያስችል ጠቁመው፤ ፌስቲቫሉ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚሰባሰቡበት አጋጣሚን ይፈጥራል ነው ያሉት።
የኬንያ፣ የጅቡቲ እና የሱዳን ኤምባሲ ተወካዮች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል። የውይይቱ ዋና አላማም ለፌስቲቫሉ መደረግ ያለባቸውን ዝግጅቶች ለመለየት ሲሆን፤ የመጀመሪያው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል በ2014 ዓ.ም በወዳጅነት ፓርክ መካሄዱ ይታወሳል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2017 ዓ.ም