አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልል ለበጋ መስኖ ልማት ከ15 ሺ በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸውን የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ኢንጅነር ግርማ ረጋሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮው ዓመት ከ22 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ለአርሶ አደሩ ፓንፖችን ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን ከ15 ሺህ በላይ ፓንፖችን ለማሰራጨት ተችሏል። እነዚህን በመጠቀም አርሶ አደሩ ከወንዞች፣ከሀይቆችና ከከተሩ ውሃዎች ለበጋ ለመስኖ ልማት የውሃ አማራጭ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው።
ለአርሶ አደሩ የተሰራጩት የውሃ መሳቢያ ሞተሮችም በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ነው የተናገሩት፡፡
በባህላዊ መንገድ የሚጠቀምባቸውን የመስኖ አውታሮች፤ የወንዝ ቅየሳ በመስራት። የወንዝ ውሃ ተደራሽ በማይሆንባቸው አካባቢዎች ደግሞ በተለያየ መጠን አነስተኛ የውሃ ጉድጓዶችን በማዘጋጀት እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
አብዛኛው አርሶ አደር የባህላዊ መስኖ አጠቃቀምን የሚከተል በመሆኑ በተወሰነ ደረጃ የውሃ እጥረት ይገጥማል የሚል ስጋት አለ ያሉት ኢንጅነር ረጋሳ ፤ይህንንም ለመቅረፍ በአንድ በኩል ህብረተሰቡ ውሃን በአግባቡ እንዲጠቀም ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ በሌላ በኩል አመራሩም ያሉትን የውሃ አማራጮች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል’።
ኃላፊው እንዳብራሩት፤ በዘንድሮው ዓመት በበጋ መስኖ ለማልማት የታቀደው ስንዴ ላይ ትኩረት በማድረግ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት ነው። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ማልማት የተቻለው ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነበር። ዘንድሮ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ተጨማሪ ለማልማት ሲታቀድ ከባለፈው ዓመት ልምድ በመቅሰም ሲሆን፤ ለዚህ የሚበቃ ዝግጅት ለማድረግም ሲሰራ ቆይቷል።
እስካሁን ለተዘጋጁት መሬቶች በቂ የዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በመዘጋጀቱ በግብርና ቢሮ በኩል ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ እንደሚገኘ ጠቁመው፤ በአርሶ አደሩም በኩልም ላለፉት ዓመታት የነበሩ ልምዶችን በመቀመር በበጋ መስኖ ልማት ያለው ተሳታፊነትና አጠቃቀም እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህም ሆኖ ክልሉ ካለው ስፋት አኳያ ሁሉንም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለማዳረስ የተወሰነ ክፍተት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ጠቁመው፤ ይህንንም ከግምት በማስገባት ስራው እንዳይስተጓጎል በቅርበት ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ክልሉ ከአለው የቆዳ ስፋት፤ ለበጋ መስኖ ልማት ከአለው ምቹነት፤ በውሃ ሀብት እና በመሳሰሉት አቅሞች ምክንያት የበጋ መስኖ ልማት በስፋት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2017 ዓ.ም