– በትራፊክ አደጋ የሚደርሰው የንብረት ጉዳት እየጨመረ ነው
አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የእጅ ስልክ ይዘው ሲያሽከረክሩ የተገኙ 28ሺህ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ገለጸ፡፡ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሙያና ሕዝብ ግንዛቤ ዲቪዢን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት ሶስት ወራትም 28ሺህ አሽከርካሪዎች የእጅ ስልክ ይዘው ሲያሽከረክሩ ፣ሰባት ሺህ 316 ከፍጥነት በላይ ያሽከረከሩ እንዲሁም ጠጥቶ በማሽከርከር የተያዙ 871 አሽከርካሪዎች ላይ ተገቢው ቅጣት ተላልፏል፡፡
የቴክኒክ ምርመራን ያላሟሉ ስድስት ሺህ 671 አሽከርካሪዎች ተገቢው ቅጣት የተላለፈባቸው መሆኑን ገልጸው፤ እንዲሁም 306 መንጃ ፈቃድ ሳይዙ ያሽከረከሩ ፣213 ሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ ይዘው የተገኙ ፣ 45ሺህ ቀይ የትራፊክ መብራትን የጣሱ እና 24 ሺህ የደህንነት ቀበቶ ያልተጠቀሙ አሽከርካሪዎች መከሰሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው በሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ምክንያት በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በትራፊክ አደጋ የተመዘገበው የንብረት ጉዳት 8 ሺህ 961 መድረሱን ተናግረዋል፡፡
አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ይህ አሀዝ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በቁጥር 708 ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።
በየጊዜው የሚጠፋው ህይወት ፣ የሚጎዳው አካልና የሚወድመው ንብረት የከተማችን አሳሳቢ ጉዳይ ነው ያሉት ኃላፊው፤ አደጋው በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ የኮሪደር ልማት ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመሰራት ላይ ያለው የከተማዋ የኮሪደር ልማት የአደጋው ሰለባ መሆኑን ያስታወቁት ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ በጅምር ያሉ አንዳንድ የግንባታ ቦታዎች ጭምር ውድመት እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሳሳቢውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል በየጊዜው በከተማዋ የትራፊክ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ የገለጹት ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ ሕግ ተላልፈው በተገኙ አሽከርካሪዎች ላይም ተገቢው የቅጣት ውሳኔ እየተላለፈ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በከተማችን በትራፊክ አደጋ ለሚደርሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ጉዳት መንስኤው ህግን አክብሮ ያለመንቀሳቀስ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ የተጠቀሱት የክስ አይነቶች ለትራፊክ አደጋ መከሰት ዋንኛ መንስኤ ናቸው ተብለው የተለዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ በከተማዋ በሚገኙ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣አቃቂና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ላይ ቁጥሩ የጨመረ የትራፊክ አደጋ መከሰቱን የገለጹት ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ አራዳ ክፍለ ከተማ ደግሞ ምንም ሞት ያልተመዘገበበት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ የትራፊክ መምሪያ በኩል ከክስና ቅጣት ያለፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክር እንደሚሰጥ የገለጹት ኃላፊው፤ አደጋ በሚበዛባቸው አካባቢዎችም ተጨማሪ ስምሪት በማድረግ ቁጥጥርና ክተትል እየተደረገ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡
የትራፊክ አደጋን መቆጣጠር የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ አይደለም ያሉት ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ እግረኞችንና የእምነት ተቋማትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ችግሩን ለመታደግ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2017 ዓ.ም