በዓሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን እየሰበኩ ማበጣበጥ ለሚፈልጉ አካላት ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ ነው

አዲስ አበባ፡– የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ጥቃቅን ልዩነቶችን እየሰበኩ ማበጣበጥ ለሚፈልጉ አካላት ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ በዓል ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡ በዓሉን በአርባ ምንጭ ከተማ ለማክበር ክልሉ ዝግጅቱን አጠናቆ እንግዶችን መቀበል መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበር የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እና ጥቅም በማክበር ነጠላ ትርክቶችን አስወግዶ ገዢ ትርክትን ለማስረጽ ጥሩ አጋጣሚ በሚፈጥር መልኩ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም በዓሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን እየሰበኩ ማበጣበጥ ለሚፈልጉ አካላት ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡

በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ክልሉ ዝግጅቱን አጠናቆ እንግዶችን መቀበል መጀመሩን ተናግረው፤ በዓሉ በሚከበርበት የአርባ ምንጭ ከተማ በዓሉን ታሳቢ ያደረጉ ልማቶችን የማስተካከል እና የማሳመር ስራዎች መከናወናቸውን አመላክተዋል፡፡ በከተማዋ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችም በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ላይ አሳምሮ በማጠናቀቅ ለበዓሉ ዝግጁ እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር አንድ ዓብይ ኮሚቴ እና ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን የገለጹት አቶ ጥላሁን፤ ከንዑሳን ኮሚቴዎች አንዱ የሆነው የሰላምና የጸጥታ ንዑስ ኮሚቴ የሰላሙን ጉዳይ ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር እንግዶች በሰላም በዓሉን አክብረው እንዲመለሱ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ትልቁ ትሩፋት የመሰረተ ልማቶችን ሥራ እና የልማት እንቅስቃሴዎችን የሚያነቃቃ እንዲሁም ፖለቲካዊ ስኬቶችን ይበልጥ የሚያጎላ መሆኑ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ከሀገር ውስጥ እንግዶች በተጨማሪ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች አከባበሩን እየጎበኙ በመሆኑ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍም የተከፈተው የንግድ ትርዒትና ባዛር በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን በማቅረብ ረገድ ለአምራቹ ገበያ በመፍጠር ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ በዓሉ ከታህሳስ 25 ቀን ጀምሮ በተለያዩ ኩነቶች በክልሉ መከበር ጀምሯል፡፡ ታህሳስ 25 “የወንድማማችነት ቀን” በማለት በአርባ ምንጭ ከተማ ታላቁ ሩጫ እና የህብረት ስፖርት መደረጉን አውስተው፤ ታህሳስ 26 “የአብሮነት ቀን” በሚል ስያሜ ከ32 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ባህል እና እሴቶች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን መከናወኑን አውስተዋል፡፡

ትናንት ታህሳስ 27 “የደቡብ ኢትዮጵያ” ቀን ስያሜ ተሰጥቶት ነጠላ ትርክትን አስወግዶ ገዢ ትርክትን ከማስረጽ አኳያ ተግባቦት ላይ ባተኮሩ በተለያዩ ሁነቶች እንደተከበረ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ዛሬ ታህሳስ 28 “የምክክር ቀን” ህገ መንግስቱ ስላበረከታቸው ትሩፋቶች ሲምፖዚየም ተከናውኖ ታህሳስ 29 ቀን መላው የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በተገኙበት “የኢትዮጵያ ቀን “በሚል ስያሜ ይከበራል ብለዋል፡፡

በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰብሰብ ብለው በአንድነት ስለ ሀገራቸው የሚወያዩበት “ብሔራዊ መግባባት ለሕብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ትልቅ በዓል ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በዓሉን አስመልክተውም ለመላው ኢትዮጵውያን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You