ከወርቅ ወርቅ የሆነ ገቢ

በተያዘው 2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠንም፤ ከወርቅ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም መጨመሩ ይገለጻል፡፡

በሩብ ዓመቱም ከወርቅ የወጪ ንግድ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ ከወርቅ ብቻ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱ መገለጹም ይታወቃል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በወርቅ ላይ ለታየው የገቢ ለውጥ አስተዋጽኦ ማድረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚላክ ወርቅ ለማግኘት ያቀደችውን ለማሳካት በርካታ ሥራዎች መሠራት እንደሚኖርባቸው ያመላክታሉ፡፡

የሥነ ምድር ተመራማሪው (ጂኦሎጂስቱ ) አቶ ሳዲቅ ከቢር የወርቅ ዋጋ ከውጭ ምንዛሪ ጋር አብሮ እንደሚሄድ ጠቅሰው፤ በውጭ ምንዛሪ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ ምርትንም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ቀደም ሲል ከነበረው በእጥፍ እንዲጨምር ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡ በመንግሥት በኩል በወርቅ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ እርምጃና ቁጥጥር መጠናከሩ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው ማበረታቻ ብዙ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ማድረግ ማስቻሉን ገልጸው፣ ባንኩ ወርቅ ለሚያቀርቡ አካላት ያደረገው ማበረታቻ ብዙዎች ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የሚያተጋ ነው ይላሉ፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ መጠን እንዲጨምር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ እርምጃው በሀገሪቱ ያለው የወርቅ ዋጋ ከጎረቤት ሀገራት ሳይቀር የተሻለ እንዲሆን ሳያደርገው እንዳልቀረም ያብራራሉ፡፡

አሁን ከጎረቤት ሀገራት ሳይቀር ወርቅ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት በወርቅ ላይ የሚፈጸመውን ህገወጥ ንግድ ለመቆጣጠር ወርቅ አምራች በሆኑ ክልሎች ግብረ ኃይል በማቋቋም ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡ ክልሎችም ባህላዊና አነስተኛ ወርቅ በሚያመርቱ ማህበራት ላይ ግዴታ ማስቀመጣቸውን አቶ ሳድቅ ጠቁመዋል፡፡

አንድ ማህበር በዓመት ምን ያህል ወርቅ ማስገባት አለበት የሚለው የወርቅ መጠን እንደ ግዴታ የተቀመጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማህበራቱ ይህንን ግዴታቸውን እንዲወጡ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ መሆናቸውን ያመላክታሉ፡፡

‹‹አሁን ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በእጥፍ መጨመሩ የምርት መጠን ከመጨመሩ ጋር የተያያዘ አይደለም›› ሲሉም አመልክተው፣ ወርቅ እየተመረተ በህገ ወጥና በኮንትሮባንድ ንግድ ሳቢያ ምርቱ ወደ ውጭ ሲወጣ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ የግብረ ኃይሉ ቁጥጥር እና ክልሎች ያስቀመጡት ግዴታ ለብሄራዊ ባንክ የሚቀርበውን የወርቅ ምርት በእጥፍ እንዲጨምር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

በወርቅ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ዘንድሮ ከወርቅ ወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ለማግኘት የታቀደው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደሚያስችልም አቶ ሳድቅ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ችግር የለም፤ ክምችቱም በደንብ አለ፤ በደንብ ከተሰራና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከታቀደው በላይ ሊገኝ ይችላል›› ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጋምቤላ ክልል የተገነባውን የወርቅ ፋብሪካ መርቀው በከፈቱበት ወቅት፤ ፋብሪካው የወርቅ ምርት በእጥፍ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ሌሎችም ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ከታቀደው በላይ ገቢ ለማግኘት እንደሚረዳ አመላክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በባህላዊና በአነስተኛ አምራቾችም የሚመረተው የወርቅ መጠን ቀላል የሚባል አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከፍተኛ አቅም ያላቸው አካላት በወርቅ ልማት ላይ እንዲሰማሩ ቢያደርግ በወርቅ ኤክስፖርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ በወርቅ አምራቾች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና የሚሰጠው ማበረታቻ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ወርቅ ከእስከ አሁኑም በላይ ብዙ የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝበት ተናግረው፣ መንግሥት ፈቃድ በተሰጣቸው አካላት ላይ ጭምር ጥብቅ ቁጥጥር ቢያደርግ ከዚህም በላይ ምርት ማግኘት እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡

የወርቅ ማእድን ከሚቆፈርበት ቦታ ጀምሮ ባሉ ሰንስለቶች ላይ የሚደረገው ጥብቅ ቁጥጥር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አቶ ሳዲቅ ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹እንደ ሀገር ከወርቅ እየተጠቀምን ነው ማለት አይቻልም፡፡ አሁን ካለው አምቅ አቅም 50 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው እየተመረተ ያለው፡፡ 70 እና 80 በመቶ ቢመረት ብዙ መጠቀም እንችላለን›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የባህር ዳር ዩኒቪርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር አሸብር ሰውአለ (ዶ/ር) ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ጠቅሰው፣ ለእዚህም ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ከምክንያቶቹ መካከል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ ሕገ ወጦችን ለመቆጣጠር እየተሰራ ያለው ሥራ እና በጸጥታ ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች ሥራ አቁመው የነበሩ አምራቾች ወደ ሥራ መመለሳቸው እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል፡፡

ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ ሊያመርት የሚችል አዲስ የወርቅ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩና ሌሎች በቅርቡ የሚጀምሩ መኖራቸው ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ከሚጎዱ ዘርፎች መካከል አንዱ ማዕድን ነው የሚሉት አሸብር (ዶ/ር)፣ አብዛኛዎቹ ማዕድን የሚወጣባቸው አካባቢዎች ከዚሁ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይህ ችግር እንዲፈታ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ማዕድን የሚገኝባቸውን ቦታዎች ሰፊ ጥናትና ምርምር በማድረግ መለየትና ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በዘርፉ ግልጽ የሆነና የተረጋጋ የሕግ ማሕቀፍ ሊኖር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በእጥፍ እንዲጨምር ከማድረግ በዘለለ የማዕድን ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚሉት አሸብር (ዶ/ር)፤ ሕገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ከተደረገ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ወርቅ የታቀደውን የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ እንደጠቆመው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማዕድናት ምርታማነትን በተለይ የወርቅ ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ነው። ማሻሻያው በአነስተኛ ደረጃ ይመረት የነበረውን የማዕድን ምርት በከፍተኛ መጠን እያሳደገው ነው፤ በተለይም የወርቅ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ ይገኛል፡፡

ሚኒስቴሩ በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ነጥብ ስድስት ቶን ወርቅ ለማምረት አቅዶ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ የእቅዱን 70 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡ ማሻሻያው የማዕድናት አምራቾችን ተጠቃሚ በማድረጉ አምራቾቹ የተሻሉ ማሽነሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ገዝተው ወደ ምርት ሥራ እየገቡ ናቸው።

በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ መጠን ጨምሯል፤ በሩብ ዓመቱ ባለፈው በጀት ዓመት ዓመቱን ሙሉ ወደ ባንኩ ከገባው አራት ቶን በእጅጉ የላቀ ሰባት ቶን ወርቅ መግባቱ ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወርቅ ላይ ከፍተኛ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ በ2017 በጀት ዓመት ከወርቅ ብቻ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን  ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You