አዲስ አበባ፡- የግብርና ሚኒስቴር የገዛቸው አምስት አውሮፕላኖች የአንበጣ መንጋን፣ የግሪሳ ወፍንና ድንበር ዘለል የሆኑ ተባዮች በሰብል ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ከመከላከል አኳያ ትልቅ አቅም ፈጥረዋል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ሚኒስቴሩ ቀደም ሲል የገዛቸው አምስት አውሮፕላኖች ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ አውሮፕላኖቹ የጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በማካሔድ የሰብል ምርቱን ከአንበጣ መንጋ እና ከግሪሳ ወፍ በመከላከል ረገድ ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ድንበር ዘለል የሆኑ ተባዮችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚናቸውን እየተወጡ ነው፡፡
ሚኒስትሩ ግርማ (ዶ/ር)፤ በአንድ ወቅት በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ኢትዮጵያን የአንበጣ መንጋ አጋጥሟት እንደነበር አውስተው፤ በወቅቱ የአንበጣውን መንጋ ለመከላከል የሚያስችል ጸረ ተባይ ኬሚካል የሚረጭ አውሮፕላን ባለመኖሩ ኢትዮጵያ አውሮፕላኖችን ከደቡብ አፍሪካ ጭምር በኪራይ መልክ አስመጥታ ትጠቀም እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች፤ ይህች ትልቅ ሀገር አብዛኛው ኢኮኖሚዋ የተደገፈው ግብርና ላይ ነው፡፡ ይሁንና የአንበጣ መንጋ፣ የግሪሳ ወፍ እና መሰል ችግር ሲያጋጥም በቶሎ ለመከላከል የሚያስችል ጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት የሚያከናውን አውሮፕላን የሌላት እንደነበረች ገልጸው፤ አውሮፕላኑን ከሌላ ሀገር ማስመጣቱ ሌላ ተጨማሪ ወጪ ሲያስወጣ የቆየ ነበር ብለዋል፡፡
ይሁንና ለኬሚካል ርጭት የሚያስፈልገውን አውሮፕላን ለማግኘት ብዙ ወጪ እያወጡ ሌላ ሀገር ሔዶ ማምጣቱ አዋጭ ባለመሆኑ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ችለናል ያሉት የግብርና ሚኒስትሩ፤ የተገዙትም ዘመናዊ የሆኑ አምስት አውሮፕላኖች በአሁኑ ወቅት ለሚደርሰው ችግር በቀላሉ መጠቀም እያስቻሉ በመሆኑ እፎይታን ማስገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
እንደ ግርማ (ዶ/ር) ገለጻ፤ አውሮፕላኖቹ በተገዙ ወቅት ከኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በመሆን ሥራ ካስጀመሯቸው በኋላ ከግብርና ሚኒስቴር ሥራ ባለፈ ለንግድ አገልግሎት ሁሉ መዋል እንዲችሉ ተደርገዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ በቅርቡ የምርጥ ዘር ድርጅቶች የኬሚካል ርጭት አካሂደውበታል፡፡
አውሮፕላኖቹ ሌሎችንም ተዛማጅ ሥራዎችን እየሠሩ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአየር ንብረቱ እንደሚያመላክተው ከፍተኛ ተባይ የሚፈጠርበት ወቅት ነውና አውሮፕላኖቹ በመኖራቸው ኢትዮጵያም ለዚያ ራሷን አዘጋጅታለች ማለት ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ አኳያ የራሷን አቅም የፈጠረች በመሆኑ ይህም እንደ አንድ ቴክኖሎጂ የሚታይ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሜካናይዜሽን፣ ከግብዓት፣ ከምርጥ ዘር አቅርቦት አጠቃላይ ከሰብል ጥበቃ አንጻር ግብርናውን ለማዘመን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ አቅርቦቶች ለማሟላት እየተሰሩ እንደሚገኙ አመልክተው፤ ይህ ግን በቂ አይደለም፤ እያደገ መሔድ አለበት፡፡ ይሁንና ጅምሩ መልካም የሚባል ነው በማለት ግርማ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ግብርና ሚኒስቴር፣ በአንበጣ መንጋ እና በግሪሳ ወፍ አማካይነት በሰብል ምርት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችሉ አምስት አውሮፕላኖችን ከገዛ ወራት መቆጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ አውሮፕላኖቹ የሰደድ እሳትን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር ላይ እንደሚሰማሩ መነገሩ ይታወሳል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም