የአባቷን ፈለግ የተከተለች – የዱዋላ ሌዘር መስራች

ወጣት ረድኤት እጅጉ ትባላለች። ትውልድ እና እድገቷ አዲስ አበባ ነው። ገና ጀማሪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ናት። የወጣትነት ጊዜዋን ውድነት ቀድማ የተረዳችው ትመስላለች።

ተማሪዎች የመሰናዶ የትምህርት ጊዜ ቆይታቸውን አጠናቅቀው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲገቡ ሰፊ የሚባል ጊዜ ይኖራቸዋል። ትምህርታቸው ላይ የሚኖራቸውን ውጤት ጥሩ ለማድረግ ሲሉም ሙሉ ለሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርታቸው ይሰጣሉ።

ወጣት ረድኤት እጅጉ በዛሬው የወጣቶች ገጻችን የነበራትን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ስለመሰረተችው የራሷ ስራ እና አሁን ስላለበት ደረጃ አጋርታናለች። የእጅ ሙያ ባደገችበት ቤተሰብ ውስጥ የሚበረታታ ነው። በመሆኑም ወደ እዚህ ስራ ስትገባ ከወላጆቿ ጥሩ ድጋፍን አግኝታለች።

ረድኤት፣ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቅቃ ሀገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ወስዳ እረፍት ላይ ነበረች። የሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ሰፊ የሚባል የእረፍት ጊዜ ነበራት። ታዲያ በዚህ ወቅት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ውጤታቸውን በጉጉት በመጠበቅ፣ ራሳቸውን በማዝናናት እና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲገቡ ይበልጥ ሊያግዟቸው የሚችሉ ትምህርቶችን በመማር ያሳልፋሉ። ረድኤት በዚህ ወቅት ቀድሞ ወደአዕምሮዋ የመጣው ምን ልስራ የሚለው ሀሳብ ነበር።

‹‹ወደእዚህ ስራ ልገባ የቻልኩት አባቴ ከቆዳ የሚሰሩ ጃኬቶችን ይሰራ ነበር ። በቤት ውስጥ ሙያውን በጥቂቱ አውቀው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ብዙም ያልተለመደውን ለምን አልሰራም? የሚል ሀሳብ መጣልኝ።›› ትላለች። ከወላጅ አባቷ የወሰደችው ጥቂት ትምህርት ላይ በተቋም ደረጃ ስልጠና ወደሚሰጡ ማዕከላት ሄዳ ችሎታዋን ለማዳበር ወሰነች ።

የተለያዩ ቦርሳዎችን በማምረት እና ለገበያ በማቅረብ ስም ያተረፉ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው። ቦርሳ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው የሚገለገሉበት ነው። ይህንን ክፍተት የተረዳችው ረድኤት የተለያየ ዲዛይን ያላቸውን ቦርሳዎች በሰዎች ፍላጎት ላይ ተመስርታ በመስራት ስራዋን ለመጀመር ወሰነች።

‹‹ቦርሳ ለሴት ልጅ በጣም ወሳኝ ነው። እኔም በጣም እወዳለሁ። ቦርሳ እንደ ፋሽን በሀገራችን ውስጥ ገና ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ነው።›› የምትለው ረድኤት፣ ሴቶች በማንኛውም ከቤት ውጪ ባለ እንቅስቃሴያቸው ቦርሳቸው አይለያቸውም። የሚይዙት ቦርሳም ያለው አገልግሎት ሊይዙት የሚፈልጉትን እቃ ከመያዝ ያለፈ ነው። ለሥራ፣ ለጉዞ እንዲሁም ለተለየ ፕሮግራም የሚያዘው ቦርሳ የተለያየ ነው። ከቤት ለመውጣት ያሰበች እንስትም እንዲሁ ያላትን ቦርሳ ይዛ አትወጣም። ከምትለብሰው ልብስ፣ ከምትገኝበት ኹነት ጋር የሚሄደውን ቦርሳ መርጣ ትይዛለች።

ባላት የእረፍት ጊዜ ተጠቅማ የምትፈልገውን ስልጠና ከወሰደች በኋላ በቤቷ ውስጥ በመሞከር ወደሥራው ገባች። ‹‹ቤተሰቦቼ ሙያ ያለው ሰው ወድቆ አይወድቅም ብለው ስለሚያምኑ አበረታተውኛል።›› በማለት የምትገልጸው ረድኤት፣ ሥራዋን በጀመረችበት ወቅት የቅርብ የምትላቸው ሰዎች ቦርሳዎችን እንደማበረታቻ እንድትሰራላቸው ይጠይቋት እንደነበር ታስታውሳለች።

ቀኑ ደርሶ የ12ኛ ክፍል፣ ሀገር አቀፍ ፈተና ይፋ ከተደረገ በኋላ ቀጣዩ ሒደት ተማሪዎች የተመደቡበትን የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ማወቅ ነው። ‹‹ የተመደብኩት ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ነበር። በወቅቱ የነበረው የጸጥታ ሁኔታ ከባድ ስለነበር እዚሁ ለመማር ወሰንኩ ።›› ስትል ትናገራለች።

አሁን ላይ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ ናት ። በኮሜርስ በምሽት መርሀግብር እየተማረች ቀን ቀን ደግሞ ሥራዋን ለመስራት ወሰነች። ‹‹ዱዋላ ሌዘር ›› የሚል ስያሜንም ሰጥታዋለች። ቃሉ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል የቤንች ቋንቋ ሲሆን፣ ‹‹በልዩነት ውስጥ አንድነት›› የሚል ትርጉም እንዳለው ታስረዳለች።

‹‹ዱዋላ ሌዘር›› የተሰኘ ከቆዳ የሚሰሩ የተለያዩ ቦርሳዎችን በሰዎች፣ በደንበኞቿ ምርጫና ፍላጎት ማለትም ‹‹custom made›› ትሰራለች። በተጨማሪም ሰዎች ተጠቅመውባቸው ያረጁ፣ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ቦርሳዎችን በተለየ መንገድ በማደስ በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጡ ታደርጋለች።

ከቆዳ የሚሰሩ ቦርሳዎችን የሰዎችን ምርጫ ተከትሎ በትእዛዝ መስራት በኢትዮጵያ ብዙም አልተለመደም። በመሆኑም በሰዎች ዘንድ ያለው ተቀባይነት ጥሩ መሆኑን ትገልጻለች።

‹‹ስጀምረው ሰዎችን ማሳመን እና ደንበኛ ማግኘት በጣም ከባድ ነበር። በሂደት ግን የተለያዩ ቦርሳዎችን ለመስራት ችያለሁ።›› በማለት ገልጻ፤ ሥራዋን በጀመረችበት ወቅት የቅርቧ የምትላቸው ሰዎች እና ቤተሰቦቿ ሥራዋን ለማበረታት እንድትሰራላቸው ያደርጉ እንደነበር አስታውሳለች።

ሰዎች በፎቶ አይተው የወደዱትን ማንኛውንም እቃ በአካል ሲመለከቱት የሚኖራቸው ምላሽ ተመሳሳይ አይሆንም። ታዲያ እዚሁ በሀገር ውስጥ በፎቶ ያዩትን ልክ ሆኖ ሲያገኙት በእርግጥም በሀገር ውስጥ የተሰራ መሆኑን እንደሚጠራጠሩ ረድኤት ገጠመኟን ታስታውሳለች።

ከቆዳ የሚሰሩ ቦርሳዎችን በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ ዋና ግብዓቱ የሆነው ያለቀለት ቆዳ እና ቦርሳ ለመስራት የሚፈልጉ ዚፕ፣ ማንጠልጠያ፣ ቁልፎች እና ማስዋቢያ ጌጣጌጦች በአብዛኛው ከሀገር ውጭ የሚመጡ ናቸው።

‹‹ግብዓቶቹን ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም እኔ የምሰራው ሰዎች ያዘዙትን ቦርሳ በሚፈልጉት የቆዳ ቀለም አይነት ነው። በማላገኝበት ጊዜ ደንበኞቼን ሌላ አማራጭ እንዳለ እነግራቸዋለሁ። ማስዋቢያ እና ጌጣጌጦችም ከውጭ ስለሚመጡ ዋጋቸው ውድ ነው ።›› ስትል ትገልጽና እነዚህም በሥራዋ የምታስተናግዳቸው ችግሮች መሆናቸውን ታብራራለች። በተጨማሪም ረድኤት፣ አነስተኛ የሆነ በራሷ የምታንቀሳቅሰው ቢዝነስ በመሆኑ የምትጠቀማቸውን ግብዓት የምትገዛው በአነስተኛ መጠን ከሚያቀርቡ አከፋፋዮች ነው። እነዚህን በገበያው ውስጥ ለማግኘት አስቸጋሪ የሆኑ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራ ለመስራት የሚያስችሉ ጥሩ ባለሙያዎች መኖራቸውንም ረድኤት ትገልጻለች።

‹‹ብዙ ሰዎች ደውለውልኝ ግን በትክክል ይመጣል ብለው ይጠይቁኛል። እኔ ግን በቆዳ ላይ ከመስራቴ በፊት በሴንቴቲክ ላይ ትክክለኛውን ለማምጣት በተደጋጋሚ እሞክረዋል። ሰርቼ ስጨርስ ካልወደዱት ደግሞ መልሼ አስተካክለዋለው ።›› በማለት ትገልጻለች።

‹‹ደንበኞቼ መጀመሪያ የሚፈልጉትን አይነት ቦርሳ ዲዛይን ፎቶ ይልኩልኛል። እኔም ለቦርሳው የሚሆነውን የቆዳ አይነት አማራጭ አሳያቸዋለሁ። ከመረጡ በኋላ የሚያስፈልጉኝን እቃዎች አሟልቼ ወደ ሥራ ገባለሁ። ›› የምትለው ረድኤት፣ ተሰርቶ እስኪጠናቀቅም ከ10 እስከ 15 ቀን ጊዜ እንደሚወስድ ገልጻለች።

ረድኤት ሥራዎቿን በአካባቢዋ ለምታውቃቸው ሰዎች በመስራት እና በማስተዋወቅ የምትሰራ ሲሆን፣ በቅርቡ የራሷን ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ከፍታ የምትሰራቸውን ሥራዎች በማስተዋወቅ ጥሩ ደንበኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት ችላለች። የሌሎች ደንበኞቿን ፍላጎት ወደ ሥራ ከምትቀይራቸው ቦርሳዎች ባሻገር አሁን ላይ የራሷን የቦርሳ ዲዛይኖች በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።

ለዚህም ፈጣሪዋን እና በሥራዋ የደገፏትን ወላጆቿን ታመሰግናለች። በቅርቡም አንድ መድረክ ላይ የራሷን ዲዛይኖች ይዛ እንደምትቀርብ ትገልጻለች። ‹‹ዱዋላ ሌዘር ከተመሰረተ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። ሰዎች ዘንድ ያለው ተቀባይነትም ጥሩ ነው።›› ትላለች።

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባትን የሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት በመጠባበቅ ላይ ሆና የፈጠረችው ቢዝነስ አሁን ላይ ደንበኞችን ከማፍራት ባለፈ በተለያዩ ትልልቅ መድረኮች ላይ የራሷን ዲዛይኖች ይዛ እንድትቀርብ አስችሏታል። ወደፊትም ለማሳካት የምታቅዳቸው ሕልሞች አሏት።

‹‹የወደፊት እቅዴ በሀገራችን ውስጥ ብዙም ትኩረት ያልተደረገባቸውን ሰፌድን እና ቆዳን አንድ ላይ በማድረግ፣ የሀገራችን ልዩ ልዩ ጥለቶችን በመጠቀም፣ ከቀርከሀ የሚሰሩ ቦርሳዎችን ለመስራት አስባለሁ።›› የምትለው ረድኤት፣ የተለያዩ ቦርሳን የሚያስውቡ ጌጣጌጦች ከውጭ የሚመጡ እና ውድ በመሆናቸው እዚሁ በሀገር ውስጥ የሚሰሩ ጎበዝ ባለሙያዎች ጋር መስራት ሌላኛው ሀሳቧ ነው።

ወጣቷ ዲዛይነር ረድኤት፣ በቅርቡም ልክ እንደቦርሳው በሰዎች ምርጫ ላይ ያተኮሩ ከቆዳ የሚሰሩ ጫማዎችን መስራት እንደምትጀምር ገልጻለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You