– በአዲስ አበባ የሚገኙ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች ቁጥር ወደ 137 አድጓል
አዲስ አበባ:- በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው አዲስ መነቃቃት መፍጠሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች ቁጥር 137 ከፍ ማለቱም ተገልጿል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው አዲስ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡ ይህም ይበልጥ የኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ለመሆን ሰፊ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከዘጠኝ ሀገራት በላይ የተውጣጡ በድምሩ ከ20 በላይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሠማራት ጉብኝት አድርገዋል ያሉት አምባሳደር ነብያት፤ በኢነርጂ መሠረተ-ልማት ፣ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ የማዕድንና የቱሪዝም ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው ብለዋል፡፡
በኢንቨስትመንትና ምጣኔ ሀብት ረገድም አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከፈረንሳይ እና የአውሮፓ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን በመግለጽ፤ የኢትዮጵያና የፈረንሳይን አጋርነት ማጠናከር የሚያስችሉ በትምህርት፣ ኢንቨስትመንት፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሊ የሱፍ አሕመድ አል-ሻሪፍ ጋር መወያየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከእስያ መሠረተ-ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኩን ጋር በኢትዮጵያና በባንኩ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ 24 የውጭ ሀገራት አዳዲስ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤቸውን መቀበላቸውን የገለጹት አምባሳደር ነብያት፤ አምባሳደሮቹ ሀገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሠሩ መግለጻቸውን ተናግረዋል። ኮሎምቢያ አዲስ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ለመክፈት ዝግጅት እያደረገች መሆኑን በመግለጽ፤ አዲስ ኤምባሲዋን ለመክፈት የምትገኘው ኮሎምቢያ አምባሳደርም የሹመት ደብዳቤያቸውን እንዳቀረቡ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች ቁጥር ወደ 137 ከፍ ማለቱን በመግለጽ፤ መዲናዋ የዲፕሎማሲ መዲናነቷና ተፈላጊነቷ እየጨመረ ለመምጣቱ ማረጋገጫ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሁለት ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የ9 ሀገራት ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ጉብኝቶቹ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ተሰሚነት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በመዲናዋ ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ለጉባኤው ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ከማይናማርና በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም