የሪል ስቴት አልሚዎች ከእንግዲህ 80 በመቶ ያልተጠናቀቀ ቤት ማስተላለፍ አይችሉም

– ምክር ቤቱ ሦስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ

አዲስ አበባ፡- በአዲሱ አዋጅ የሪል ስቴት አልሚ ድርጅቶች ያለደንበኛው ፍላጎትና ፈቃድ አጠቃላይ ግንባታው ቢያንስ 80 በመቶ ያልተጠናቀቀ ቤት ለደንበኞች ሊያስተላልፉ እንደማይችሉ የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ትናንት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ሦስት ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል።

የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር)፤የሪል እስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የሪል እስቴት ልማቱ አቅርቦት እጅግ ወደኋላ የቀረና የሕዝቡን ፍላጎት የማያሟላ በመሆኑ፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ግመታ ሥርዓቱ ዘመናዊና በመረጃ በተደገፈ መልኩ ተገማች ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ በማስፈለጉ እና በማይንቀሳቀስ ንብረት ገበያው ግልጽነት መጓደሉ የኢኮኖሚ መዛባት እያስከተለና የመንግሥትን ጥቅም የሚያሳጣ እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ አዋጅ የሪል ስቴት አልሚ ድርጅት ያለደንበኛው ፍላጎትና ፈቃድ አጠቃላይ ግንባታው ቢያንስ 80 በመቶ ያልተጠናቀቀ ቤት ለደንበኞች ሊያስተላልፍ እንደማይችል አስቀምጧል ብለዋል።

በተጨማሪ በሪል ስቴት ልማት ላይ የሚሳተፍ ማንኛውም አካል የውሸት ማስታወቂያ ማስነገር  እንደማይችልም ደንግጓል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 ሆኖ በሁለት ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

በተመሳሳይም እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕንፃዎች ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በማብራሪያቸውም፤ ረቂቅ አዋጁ በነባሩ ሕግ በአፈፃፀም የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ፣ የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት የሚያረጋግጥ፣ የግንባታ ጥራትና የሀብት ብክነት ችግሮችን ይቀርፋል፡፡

በተጨማሪም ግልጽና ለአተገባበር ምቹ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ የኢትዮጵያ ሕንፃዎች አዋጅን፤ አዋጅ ቁጥር 1356/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ማሻሻያ አዋጅን ለማጽደቅ የቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አዳምጧል፡፡

ሰብሳቢው በማብራሪያቸው፤ የውሳኔ ሃሳብ ኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ለመተግበር የሚያስፈልጉ ደንብና መመሪያዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ውክልና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አለመስጠቱ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ተፈፃሚ ለማድረግ ተቋሙ መቸገሩንና የተቋሙ ሥራ መጓተቱን ቋሚ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

በመሆኑም ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን ከመረመረ በኋላ አስፈላጊነቱን በሙሉ ድምፅ የተቀበለው መሆኑን ጠቁመው፤ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው የረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ከተወያየ በኋላ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ማሻሻያ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1358/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም

Recommended For You