የሀገሪቱ የዲጂታል ልማት ወደ አስተማማኝ ደረጃ እያደገ ነው

አዲስ አበባ፡- የሀገሪቱ የዲጂታል ልማት ወደ አስተማማኝ ደረጃ እያደገ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) 2ኛው ሀገራዊ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ትናንት በአዲስ አበባ ሲከፈት እንደገለጹት፤ በዲጂታል መታወቂያ እና የዲጂታል ክፍያዎች ለማስፋፋት በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የሀገሪቱ የዲጂታል ልማት ወደ አስተማማኝ ደረጃ እያደገ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

እነዚህ የልማት ሂደቶች የኢትዮጵያን ዲጂታል ራዕይ ለመደገፍ እና ዘላቂ እና የማይበገር የዲጂታል መሠረተ ልማት እድገትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማሕቀፎች የዲጂታል ልማቱን ለማሳካት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፤ በወሳኝ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ እንዲሁም በርቀት የሚገኙ አካባቢዎችን በማስተሳሰር እና በተለያዩ የኃይል አማራጮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የዲጂታል ዘርፉ ሁሉን አሳታፊ፣ ጤነኛ እና ዘላቂ እድገት እንዲኖረው የሚያስችሉ በርካታ የህግ ማሕቀፎች ወጥተው ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ተናግረዋል።

የግሉ ዘርፍም የዳታ ማዕከላትን በማስፋፋት እና አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ እያደረገ ያለው ተነሳሽነት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግሥት የጀመረውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አጠናክሮ በማስቀጠል የዲጂታል እድገቱን አሳታፊ እና አካታች ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል። ስንተባበር ለወደፊቷ ዲጂታል ኢትዮጵያ አዳዲስ እድሎችን መፍጠር እና ችግሮችን መፍታት እንችላለን ያሉት ዶክተር በለጠ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዳበረ ዲጂታል ስነ-ምህዳር ለመፍጠር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አመላክተዋል፡፡

አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ የዲጂታል እውቀት ያለውን ወሳኝ ድርሻ በመረዳት መንግሥት በተለይ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮግራም በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ መካሄድ ፖሊሲዎችን ለማጠናከር፣ የአቅም ግንባታ ውጥኖችን ለማሳካት እና የባለብዙ ባለድርሻ አካላት ትብብርን ለማጎልበት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በይነ መረብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ያለው ሚና እየጨመረ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የበይነ መረብ አስተዳደር፣ ተጠያቂነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለሀገር እድገት ወሳኝ ናቸው ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ለምታደርገው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አስተማማኝ እና አካታች የበይነ መረብ አስተዳደር ወሳኝ መሆኑን እንገነዘባለን ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም

Recommended For You