በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 146 ሺህ 686 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዷል

– 4 ሺህ 449 ሄክታሩ በበጋ መስኖ ስንዴ የሚሸፈን ነው

አዲስ አበባ፡- በ2017 የበጋ መስኖ ልማት 146 ሺህ 686 ሄክታር መሬት በማልማት 35 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ ከዚህ ውስጥ አራት ሺህ 449 ሄክታር መሬቱ በበጋ መስኖ ስንዴ የሚሸፈን መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓለምይርጋ ወልደሥላሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2017 የበጋ መስኖ ልማት በሁለት ዙሮች በሆርቲካልቸርና በአዝዕርት ሰብሎች 146 ሺህ 686 ሄክታር መሬት በማልማት 35 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ከዚህ ውስጥም አራት ሺህ 449 ሄክታር መሬቱ በበጋ መስኖ ስንዴ የሚሸፈን ነው ብለዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት በክልል፣ በዞን፣ በወረዳ እንዲሁም በቀበሌ ደረጃ የንቅናቄ መድረኮችን በማካሄድ እቅዱን የጋራ የማድረግ እና የመግባባት ሥራ ተሠርቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል ያሉት አቶ ዓለምይርጋ፤ ከዚህ ጎን ለጎንም የውሃ አማራጮችን የመለየት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን ድረስ 68 ሺህ 311 ሄክታር መሬት መታረሱን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 49 ሺህ 521 ሄክታር መሬትም ማልማት ተችሏል ብለዋል፡፡

ለበጋ መስኖ ልማት አርሶ አደሩ ከመኸር እርሻ የተረፈውን ግብዓት እየተጠቀመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተገኘውን 10 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ መስኖ ቀድመው ለሚዘሩ አርሶ አደሮች እንዲደርስ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

በተወሰነ መልኩ እጥረቶች ቢኖሩም ተጨማሪ ግብዓት ለማቅረብም እንደሀገር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የግብርና ሥራ የሁሉንም ባለድርሻዎች ተባብሮ መሥራት የሚጠይቅ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉም ሥራዎች ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች የየድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አቶ ዓለምይርጋ ወልደሥላሴ ጠይቀዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You