‹‹መሪነት ሀገርን ከድህነት ወደ ብልፅግና የማሻገር የትውልድ አደራ ነው›› – አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- መሪነት ለትውልድ መሥራት ነው፤ ሀገርን ከድህነት ወደ ብልፅግና የማሻገር ርዕይ ያነገበ የትውልድ አደራም ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ‹‹ነጸብራቅ›› የመሪነት ኮንፍረንስ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ትናንት በተካሄደ ወቅት እንደገለጹት፤ መሪነት ለትውልድ መሥራት እንደሆነ እና ሀገርን ከድህነት ወደ ብልፅግና የማሻገር ርዕይ ያነገበ የትውልድ አደራ ነው፡፡ የአመራር ከፍተኛው ጥራትም ታማኝነት ነው፤ አመራሩ ለራሱ፣ ለሕዝቡና ለሀገሩ ታማኝ መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

በመሪነት ኮንፍረንሱ ነባር አመራሩና ተተኪ አመራሩ ተሞክሮ ሲለዋወጡ መናበብ እንደሚፈጠር ገልጸው፤ አመራር ከተናበበ አንድ የአመራር ትውልድ የጀመረውን ሌላው የአመራር ትውልድ ይጨርሰዋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በረዥም የታሪክ ምእራፍ ውስጥ አልፎ አልፎም ቢሆን ታላላቅ መሪዎችን አግኝታለች ያሉት አቶ ጥሩነህ፤ አመራሮቹን የሚተካቸው ጠፍቶ በአንድ ወቅት ብቅ ብለው የጠፉና ሊደገሙ የማይችሉ የጋን መብራት ሆነው ማለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ይህንን አደራ የተቀበሉ ያላቸውን እውቀትና ክህሎት ሳይሰስቱ ጥቅም ላይ አውለው እዚህ አድርሰውታል ብለዋል፡፡ ቅብብሎሹን ለማስቀጠልና መንገዳችንን በመደመር ጉዞ ለማጽናት ቀሪው የዚህ ትውልድ ሥራ እንደሆነም አሳስበዋል፡፡

ዛሬ የተጀመሩት ንቅናቄዎችና የብልፅግና ሥራዎች ሁሉ ሊሳኩና ፍሬ ሊያፈሩ የሚችሉት የሚተክል፣ የሚያጠጣ ፣ የሚያሳድግ፣ የሚንከባከብና የሚሰበስብ አመራር በየዘመኑ ሲፈጠር እንደሆነም ጠቅሰዋል። እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመጓዝ ዘመኑ የሚጠይቀውን የመሪነት ትጥቅ መታጠቅ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ነጸብራቅ የመሪነት ኮንፍረንስም የመጣንበትን፣ ያለንበትንና የወደፊት መዳረሻችንን እንዲያመላክት ታስቦ የተቀረጸ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ በተለያየ የሥራ መስክ ላይ ሆነን ያገኘናቸውን ልምዶች በማቀናጀት፣ ችግርን ወደ መልካም አጋጣሚ የቀየርንባቸውን ተሞክሮዎች በማጋራት፤ የመሪነት ጥበባችንን ለመለዋወጥ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ነጸብራቅ የመሪነት ኮንፍረንስ እንደስሙ ሃሳቦች የሚንጸባረቁበት እንደሆነና በዲጂታል ዘመን የአመራሩን የተለየ ሚና ለመመልከት የሚያስችል ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ለሀገር ግንባታ በተለያየ ቦታ ላይ ያሉ አመራሮች ሚናም ምን መሆን እንዳለበት የሚመከርበት ኮንፍረንስ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በወጣቶችና በሴቶች ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች እና በመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ኮንፍረንሱ ጊዜ ወስዶ የሚመክር እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የህብረተሰቡን ድንቅ ሃሳብና ተግባር ተከትላ ትልም እንደምታስቀምጥና በብቁ አመራርና የህብረተሰብ ተሳትፎ ወደ ተግባርም እንደምትቀይር አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡

ኮንፍረንሱ ከሀገሪቱ ከሁሉም ማዕዘናት የመጡ ልዩ ልዩ አመራሮችን ያቀፈ መሆኑ አድማሰ ሰፊና ደርዘ ብዙ ያደርገዋል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞች ጋር በቀጣይ ለሚመክረው ጉባዔም እርሾ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You