አዲስ አበባ፡- የጥጥ ልማቱንና ኢንዱስትሪው በዘላቂነት በቀጥታ ተሳስረውና ተናበው እንዲሄዱ የጥጥ ኮንትራት እርሻ ለማስፋት ርብርብ እያደረገ እንደሚገኘ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳምሶን አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት ምቹና ተስማሚ አግሮ ኢኮሎጂ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ በተለይም ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሌ፣ አፋር ክልሎች፣ የአማራ ክልል ምእራብ ጎንደርና የመሳሰሉት አካባቢዎች እንዲሁም ኦሮሚያ ላይ ከፍተኛ ጥጥ ማምረት የሚያስችል አቅም አላት፡፡
በኢትዮጵያ የአሠራር ሥርዓቶችን በማዘመን የጥጥ ኮንትራት እርሻን ለማስፋፋት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የጥጥ ልማቱን ከኢንዱስትሪው ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር ከልማቱ የበለጠ ለመጠቀም በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ጥናቶችም ሀገሪቱ ጥጥ በዝናብም በመስኖም ሊለማባት የሚያስችል ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዳላት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ እስካሁን ማልማት የተቻለው ግን ከ100 ሺ ሄክታር አይበልጥም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
ከአነስተኛ እስከ ሰፋፊ እርሻዎች በጥጥ ልማት በቀጥታና በተዘዋዋሪ በየዓመቱ እስከ ሁለት ሺህ የሚደርሱ አልሚዎች እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፣ በየዓመቱ ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች በጥጥ ልማት እንደሚተዳደሩ ጠቁመዋል፡፡ ካለው እምቅ አቅም አኳያ በዘርፉ ተጠቃሚ የሆነው ዜጋ ቁጥር አነስተኛ የሚባል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በአንፃሩ እንደ ቻይና፣ ብራዚልና አሜሪካ ያሉ ሀገራት ከጥጥ ልማት ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ እንደሚያገኙ ጠቅሰው፤ እነዚህ ሀገራት ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን ዜጎቻቸው የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ሀገሪቱ ያላትን ጥጥ የማምረት አቅም ሥራ ላይ ለማዋልና ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አቶ ሳምሶን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ምርታማነቱን ከማስፋትና በጥራት፣ በመጠንና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የጥጥ አቅርቦት እንዲኖር ከማስቻል በዘለለ ከኢንዱስትሪው ጋር ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ከክልሎችና ከመመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው›› ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በሀገሪቱ እየተመረተ ያለው ጥጥ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ አይደለም፤ በዚህ ምክንያት ጥጥ ከውጭ እንዲመጣ እየተደረገ ነው፡፡ ‹‹ሚኒስቴሩ ከምርምር ተቋማት ጋር በመሆን የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ለተጠቃሚዎች ለማድረሰ ጥረት እያደረግ ይገኛል። በተለይ አነስተኛ ማሳ ላላቸው አርሶ አደሮች የጥጥ አምራረት ኤክስቴንሽን እውቀትን የማሳደግ፣ ዘር ብቻ ሳይሆን ሌሎች የኬሚካል ግብዓቶችን በማቅረብ ምርታማነታቸው እንዲጎለብት እየተሰራ ነው፡፡
እንደ አቶ ሳምሶን ገለጻ፤ ጤናማ ባልሆነ የግብይት ሥርዓት ምክንያትና ተገቢው የግብይት ትስስር ባለመፈጠሩ ምክንያት ጥጥ አምራቹ ከፍተኛ የሆነ የገበያ ስጋት ስላለበት በስፋት ለማምረት ይቸገራል፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር የግብይት ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን የማድረግና እርሻውና ኢንዱስትሪው ተሳስረውና ተናበው የኮንትራት እርሻ ለማስፋት ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ የመሬት ሽፋኑንም ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረት እምርታ እያመጣ ነው፡፡
በተጓዳኝም ከእርሻ እስከ ኢንዱስትሪ ድረስ ባሉ የእሴት ሰንሰለቶች ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር፤ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማርካት እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል። ‹‹የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የጥጥ ፍላጎት በመጠንም፤ በጥራትም ሆነ በዋጋ ሙሉ ለሙሉ ሸፍነን ወደ ውጭ እስከመላክ ድረስ መሄድ የሚቻልባቸው ስራዎች እየተሰሩ ናቸው›› ብለዋል፡፡
እንደ ስራ አስፈፃሚው ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ መዳመጫ የሚባል ፋብሪካ አካባቢ ካሉ 15ሺህ አርሶ አደሮች በኮንትራት ውል ወስደው በማምረት ለፋብሪካው ጥጥ እያቀረቡ ነው፡፡ በአርባ ምንጭ በሚገኙና ሌሎች የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችም በእንደዚህ አይነት ስራዎች ውስጥ እንዲገቡ የኮንትራት እርሻ ህጉን ለማስተዋወቅ፤ ስጋቶች እንዲፈቱላቸው ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ከእርሻዎቹ ጋር የኮንትራት እርሻ ልማት ውስጥ ገብተው ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግና ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ክልሎች ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አስገንዝበው፤ ‹‹ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ለማካሄድ እየሰራን ነው፤ በዚህም ላይ በጣም ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው፤ የመሬት ሽፋኑም በዚያው ልክ ጭማሬ እየታየ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያንን ስንል ግን ነገሮች ሁሉ የተደላደሉ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አሁንም በተለይ በግብይት፣ በግብዓትና በፋይናንስ አቅርቦት እንዲሁም በሰው ኃይል ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል›› ብለዋል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም