አዲስ አበባ፡- የኮሪደር ልማቱ የሚፈጥራቸው ውብና ጽዱ ከተሞች ከቱሪዝም ውጭ የሆነውን እንቅስቃሴ ወደ ቱሪዝም እንዲመጣ በማድረግ የቱሪስት ፍሰትን እንደሚጨምሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
በቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የቱሪዝም አሠልጣኝ እና ባለሙያ ዐቢይ ንጉሤ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ በሀገሪቱ ተጨማሪ የቱሪዝም አማራጭ ይፈጥራል ፤ የሚፈጠሩት ውብና ጽዱ ከተሞች ከቱሪዝም ውጭ የሆነውን እንቅስቃሴ ወደ ቱሪዝም እንዲመጣ በማድረግ የቱሪስት ፍሰትን ይጨምራሉ፡፡
ቱሪዝም በሰው ልጅ እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ ማንኛውም ልማት ለዘርፉ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ ለቱሪዝም መስህብ፣ መዳረሻ ቦታዎች፣ ትራንስፖርት፣ የማረፊያ ሥፍራዎች እና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አንኳር የሆኑ ጉዳዮች እንደመሆናቸው የኮሪደር ልማቱ እነዚህን ጥቅሞች ይዞ ይመጣል ብለዋል፡፡
አንድ ሰው ጉዞ ሲያደርግ የሚመለከተው ቦታ ውብና ጽዱ ከሆነ ቦታው በራሱ መስህብ ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ከኮሪደር ከልማቱ ጋር ተያይዞ መንገዶች እንዲሰፉ መደረጉ የትራንስፖርት መጨናነቅን ይቀንሳል፡፡ አስጎብኚዎች ቱሪስቶችን ይዘው በከተሞች ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት የትራንስፖርት መጨናነቅ ካለ ውስን የሆኑ ቦታዎችን ነው የሚያስጎበኙት ያሉት አቶ ዐቢይ፤ የመንገድ መጨናነቁ ሲቀንስ ተጨማሪ ጊዜ ስለሚገኝ ተጨማሪ ቦታዎችን ለማስጎብኘት እድል ይፈጠራል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ልማቱ የማረፊያ፣ የካፍቴሪያ እና የመመገቢያ ሥፍራዎችን ያሟላ መሆኑም፤ አንድ ሰው ጉብኝት ሲያደርግ በእነዚህ ሥፍራዎች አገልግሎት እያገኘ እንዲጓዝ ያስችለዋል፡፡ ጎብኚዎች እየተዝናኑ የእግር ጉዞ ማድረግ እንዲችሉና በሳይክል እየተጓዙ እንዲጎበኙም አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፤ ይህም ለስፖርት ቱሪዝም እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ የተሠሩት ማራኪ የመዝናኛ ሥፍራዎችና ጎዳናዎች የተለያዩ ሁነቶችን ለማዘጋጀት፤ ባህሎችን ለማስተዋወቅ፤ ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር እና የፎቶ ግራፍ ሥነ ሥርዓትን ለማከናወን እንደሚጠቅሙም ገልጸዋል፡፡ የማረፊያና የመዝናኛ ሥፍራዎቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣሉም ብለዋል፡፡
ውብና ጽዱ ከተሞች ሲፈጠሩ ከቱሪዝም ውጭ የሆነውን እንቅስቃሴ ወደ ቱሪዝም እንዲመጣ ያደርጋል ያሉት ባለሙያው ፤ በዚህም ለሥራ የመጣ ባለጉዳይ በነገሮች ተስቦ ለመጎብኘት ይገደዳል ነው ያሉት፡፡ ለምሳሌ ጎብኚዎች አዲስ አበባን በአንድ ቀን ጎብኝቶ የማጠናቀቅ እቅድ ቢኖራቸው፤ መስህቦች መጨመራቸውን ተከትሎ የጉብኝት ጊዜያቸውን ሊያራዝሙ ይችላሉ፤ ይህም ተጨማሪ ገቢ ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የባህል አማካሪው አቶ ተስፋዬ ይመር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ልማቱ ከባህልና ቱሪዝም አንጻር ያለው ሚና የጎላ ነው፡፡ ከባህል አንጻር ሲታይ የኮሪደር ልማቱ እና እየተሠሩ ያሉ የባህል ተቋማት በዘርፉ ለተሠማሩ አካላት የሥራ እድል በመፍጠር ያገለግላሉ፡፡ በሌሎች ሀገራት በመንገድ ላይ የሚደረጉ ትርኢቶች አሉ ፤ ኮሪደር ልማቱ የተሠሩ ቦታዎች የተለያዩ ኪነ ጥበባዊና ባህላዊ ትርኢቶችን ለማሳየት እንዲሁም ኤግዚቢሽኖች ለማዘጋጀት አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡
አብርሆት ቤተ መጻህፍትን ጨምሮ ቀደም ሲል ወደ ለሙ ቦታዎች ለመጓዝ የመንገድ መጨናነቅ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ የኮሪደር ልማቱ የቱሪስት ፍሰቱን ከመጨመር አንጻርም ሚናው የጎላ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም ቢጎበኙት ለአካባቢያቸው የሚሆን ልምድ ይዘው እንዲሄዱ ያስችላቸዋል፡፡ በከተማው እንደልብ የመንቀሳቀስ እድል ስለሚኖር፤ ተዝናንተው ትውስታን ይዘው መሄድ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በፊት የውጭ ቱሪስቶች ሲመጡ ከመንገድ መጨናነቅ የተነሳ ወደ መዳረሻቸው ለመሄድ ይቅርና ወደ ኤርፖርት ለመሄድ እንኳ ይቸገሩ ነበር፡፡ አሁን ግን መንገዶች ሠፍተዋል፤ የኮሪደር ልማቱም እንደመዳረሻ ሆኖ ማገልገል ችሏል፡፡ በመንገድ ዳር የሚሠሩ መጸዳጃ ቤቶችና ማረፊያ ሥፍራዎች መኖራቸውም ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ፈጠሯል ሲሉ አስተያየታቸውን ሠጥተዋል፡፡
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም