ፖለቲካ ፓርቲዎች አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ ሚናቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

– ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን አጀንዳዎች ተረከበ

አዲስ አበባ፦ ፖለቲካ ፓርቲዎች አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ ሚናቸውን እንደሚወጡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሰባት ክፍሎችና በ64 ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ያዘጋጃቸውን አጀንዳዎች ትናንት ተረክቧል።

አጀንዳዎቹን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከሌሎች ኮሚሽነሮች ጋር በመሆን በጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ከተመራው የምክር ቤቱ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ልዑክ ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል። የተደራጁት የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳዎች ለአካታችና አሳታፊ ሀገራዊ ውይይት የሚያግዙ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ ያስረከበው አጀንዳ በጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀ ነው። በዚህም ታሪክና ትርክት፣ የሀገርና የተቋማት ግንባታ፣ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎችን መሠረት ያደረጉ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ማስረከቡን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሀገራዊ ኮሚሽኑ በጋር እንደሚሠራ ገልፀው፤ በመተባበርና በመከባበር ሀገርን በጋራ እንገነባለን። በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ አደራ ሰጥቷል ብለዋል። እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ተባባሪ አካላት ናቸው። በዚህም የጋራ ምክር ቤቱ በጥልቀት ተወያይቶ ያፀደቀውን የውይይት አጀንዳ አስረክቧል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ክልሎችና ተቋማትን የሚያሳትፍ መሆኑን ገልፀው፤ የተሳታፊ ልየታ፣ መረጣና የአጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ጊዜያት የፌደራል ባለድርሻ አካላትና ተቋማት መንግሥትን ጨምሮ አጀንዳ እንዲያስረክቡ ይደረጋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች የቀሩ ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You