አዲስ አበባ፦ በሀገሪቱ ሕግና የፍትህ ተቋማት ረዥም ታሪክ ቢኖራቸውም በዘመናዊ መልክ የተደራጁ እንዳልነበሩ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አሮን ደጎል አስታወቁ።
ዳይሬክተሩ የፍትህና ሕግ ኢንስቲትዩትን እንደገና ለማቋቋም በተዘጋጀው አዋጅ ላይ የሕዝብ ውይይት በተካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ሕግና የፍትህ ተቋማት ረዥም ታሪክ ቢኖራቸውም በዘመናዊ መልክ የተደራጁ አልነበሩም።
ተቋማቱን በተመለከተ የሚሠሩ ጥናቶችም በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተካሄዱ ፤ የተካሄዱ ጥቂት ጥናቶችም ቢሆኑ በግለሰቦች እጅ እንደነበሩ አመልክተው፤ በዚህም የተነሳም ጥናቶችን መሠረት ባደረገ መልኩ የሕግ ተቋማትን በማጠናከር ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለፍትህ ተቋማት እና ለዳኝነት አካል የሚያስፈልገውን ያህል ትኩረት የተሰጠው አልነበረም ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ በተመሳሳይ ሥልጠናንም በተመለከተ ዳኞችን፤ አቃብያነ ሕግን እና በፍትህ ዘርፉ ያሉትን አካላት ብቃት በየወቅቱ እየፈተሸ አቅማቸውን የሚገነባ የተማከለ ተቋም አልነበረም ብለዋል።
ዳኞች፣ ዓቃብያነ ሕግን እና ሌሎች በፍትሕ ዘርፉ ውስጥ የጎላ ሚና የሚጫወቱ የፍትሕ አካላት በአግባቡ ሥልጠና ወስደው ተቋማትን የሚቀላቀሉበት አሠራርም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንዳልነበረ ጠቁመው፤ የፍትህና እና የሕግ ባለሙያዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቀጥታ ወጥተው ተቋማቱን ይቀላቀሉ እንደነበር አመልክተዋል።
ይህ ለፍትሕ ሥርዓቱ መዘመን እና ቀልጣፋነት እንዲሁም ተደራሽነት እና ጥራት ያለው የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ተግዳሮት እንደነበር አመልክተዋል። ከዚህ የተነሳም በፍትሕ ዘርፉ ላይ በተደራጀ ሁኔታ ጥናት እና ምርምር የሚያካሂድ ተቋም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል።
አዋጁ ሲጸድቅ የሚፈጠረው አደረጃጀት በእውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአመለካከቱ፣ እንዲሁም በሥነ-ምግባሩ ብቁ የሆነና የተሟላ ሥብዕና ያለው የዳኝነት እና የፍትህ አካላት አመራር እና ባለሙያ በማፍራት የፍትህ ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚረዳም ጠቁመዋል።
የዳኝነት፣ የፍትህ አካላትና ሌሎች ከፍትህና ሕግ ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላትን ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ ለማድረግ ጥናትና ምርምሮችን ማከናወን አስፈላጊ ነው። በዚህም ረገድ አዲሱ አደረጃጀት የሀገሪቱ የፍትህ ዘርፍ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እያሳካ ስለመሆን አለመሆኑ አስተማማኝና የተሟላ መረጃ ለመሰብሰብ እና ለማደራጀት የሚያስችል እንደሚሆንም አመልክተዋል።
ከተሰብሳቢዎች የፌዴራል ሼርያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሀመድ አዋል ሼርያ ፍርድ ቤቶች በመላው ሀገሪቱ ቢኖሩም ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት ሥልጠና አግኝተው አያውቁም። ፍርድ ቤቶቹ የፍትህ አካል እንደመሆናቸው በአባልነት እንዲካተት ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ፤ጥያቄው በማሻሻያው ምላሽ የተሰጠው መሆኑ ተገልጿል።
ተቋሙ በ1990 ዓ.ም «የፍትሕ እና የሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት » በሚል በቀድሞው የአቅም ግንባታ እና በፍትሕ ሚኒስቴር ስር ሲሠራ ነበር። ከ1995 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆኖ የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች የሥልጠና ማዕከል በመባል ለበርካታ ዓመታት ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
በ2010 ዓ.ም ሁለቱም ተቋማት አንድ ወጥ ባደረገ አደረጃጃት የፌዴራል የፍትሕ እና የሕግ ምርምር እና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ተብሎ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የፌዴራል ፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት በሚል ተቀይሮ እስከዛሬ ድረስ በዚሁ ስም እየሠራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም