አዲስ አበባ፦ የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በልማት ያስተሳሰረና የጋራ ተጠቃሚነት ተምሳሌት መሆኑ ተገለጸ። ሀገራዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው የፓርላማ የዜጎች መድረክ በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) የዓባይ ግድብ የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስን ከማጠናከር አንፃር ያለውን ሚና አስመልክተው ባቀረቡት ጽሁፍ፤ የዓባይ ግድብ የሃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራት እና አፍሪካውያንን የሚያስተሳስር የፓን አፍሪካን ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት የተገነባው ይህ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በልማት ያስተሳሰረ እና ለጋራ ተጠቃሚነት ምሳሌ የሆነ ፕሮጀክት ነው ያሉት ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ አፍሪካውያን አይችሉም የሚለውን ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ የሰበረ፤ የይቻላል ሰንደቅ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
ኢትዮጵያ በዓድዋ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን በመስበር ምሳሌ እንደሆነችው ሁሉ በዓባይ ግድብም ለአፍሪካውያን የኢኮኖሚ ነፃነት ተምሳሌት ሆናለች ብለዋል።
በመድረኩ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ምሁሩ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓባይ ጉዳይ ለዘመናት ኢትዮጵያ በርካታ ተግዳሮቶች እንደገጠሟትና እነዚህንም በጠንካራ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ሥራ እንደታለፉ ገልጸው፤ የዓባይ ግድብን ኢትዮጵያ ለፍፃሜ ምዕራፍ ማቃረቧን አስረድተዋል።
አያይዘውም ለዘመናት የቆዩ ኢ-ፍትሐዊ የናይል ወንዝ ውሎች ተሽረው የናይል የትብብር ማዕቀፍ መጽደቁን አንስተው፤ ይህም ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን አብስረዋል።
የዓባይ ግድብ ግብጽ ባደረገችው አሉታዊ ተጽዕኖ ምክንያት የውጭ ፋይናንስ እንደማይገኝለት በመታወቁ ለአፍሪካ ምሳሌ በሚሆን መልኩ በመላ ኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብትና ትብብር በስኬት መገንባቱን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ጽሁፍ አቅራቢ አምባሳደር ቶፊክ አብዱላሂ ናቸው።
በኢህአዴግ ዘመን ግድቡ ከተጀመረ በኋላ ችግር አጋጥሞት እንደነበረና በሥራው መጓተት ምክንያት 450 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ማስከተሉን አስውስተዋል። ይሁንና የለውጡ መንግሥት ግድቡን በመታደግና ተደጋጋሚ ጫናዎችን በመቋቋም ለፍሬ አብቅቶታል ብለዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ የሚወያዩበትና ሃሳባቸውን የሚያንጸባርቁበት መድረክ በተለይም በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ በመሆኑ ይህ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የመጀመሪያው መድረክ ትኩረት የዓባይ ግድብ እንደሚሆን እና በቀጣይም በየወሩ በተለያዩ አንገብጋቢና አነጋጋሪ ጉዳዮች ዙሪያ መድረኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በውይይት መድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሚዲያ አመራሮች፣ ምሁራን በመገኘት ገንቢ ሃሳቦች ሰንዝረዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም