አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የደን ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓትን ለማስፈን የሚረዳ አዲስ አሠራር ሥራ ላይ እንደሚውል ተገለጸ፡፡ የሚተገበረው አሠራር ዓለም አቀፍ የደን አያያዝና አጠቃቀም መስፈርትን (ስታንዳርድን) ከግምት ያስገባ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ የደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም እንደተናገሩት፤ የደን አስተዳደር ደረጃው የተነደፈው በኢትዮጵያ ዘላቂ የደን አያያዝና አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል ነው። አሠራሩ ሀገራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባና ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያለው እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
በደን አያያዝና አጠቃቀም ላይ ቀጣይነት ያለው አሠራርን በማረጋገጥ፣ የአካባቢ ጥበቃን ማጎልበት፣ ዓለምአቀፍ የገበያ ትስስርን መፍጠር እና ጥራት ያለው ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የደን ሀብቷን ሽፋኗን እያሳደገች እንደምተገኝ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏን ገልጸዋል። ሀገሪቱ በ2017/18 ዓ.ም 50 ቢሊዮን ለማድረስ አቅዳ እየሠራች እንዳለችም አብራርተዋል ፡፡
ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን ደኖች እንዲጠበቁና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ወቅታዊና አስፈላጊ ጉዳይ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ የደን ሀብት ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት አቶ ከበደ፤ አዲሱ አሠራር በይፋ መጀመሩም የኢትዮጵያን የደን ዘርፍ ለማሳደግ ወሳኝ ርምጃ ነው ብለዋል፡፡
አዲሱ አሠራር ደኖች ያለአግባብ እንዳይጨፈጨፉ፤ ይልቁንም ለአካባቢው ሕብረተሰብ ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ ያደርጋል፤ የጉልበት ብዝበዛን የሚያስቀርና ደኖች ዘላቂ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የደንና ዱር እንስሳት ቢሮ የደን ጥበቃና የሕብረተሰብ ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ ገነነ ኃይሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የደን ምርቶችን ጥራት በማስጠበቅ ተጠቃሚ የሆኑ 85 ሀገራትን መቀላቀሏ ጥሩ እድል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ደንን ዝም ብሎ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከላዩ ላይ በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው ያሉት አቶ ገነነ፤ ለዚህም የአሠራር ሥርዓትን አስቀድሞ ማወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ አዲስ የጸደቀው መስፈርት (ስታንዳርድ) ስላለው ጠቀሜታ እና ጥቅም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ግንዛቤ ጨብጦ ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባልም ብለዋል፡፡
የኤፍ.ኤስ.ሲ የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ ወይዘሮ አናህ አጋሻ፤ የኤፍ.ኤስ.ሲ ‹‹FSC›› ስታንዳርድ በኢትዮጵያ ደን ጥበቃ ላይ በርካታ እንድምታዎች ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስታንዳርዱን ተቀብላ ጥቅም ላይ ለማዋል መዘጋጀቷ እያካሄደች ካለችው የአረንጓዴ ልማት ሥራዋ አንጻር ተጠቃሚ ያደርጋታል ነው ያሉት፡፡
የደን ዘርፍ ሥራ አስኪያጆች፣ የመንግሥት ኤጀንሲዎች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ደረጃውን የጠበቀውን አሠራር በፍጥነት በመከተል የደን ሀብቱን ለማሳደግና ከሀብቱ ሀገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
የደን አስተዳደር ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ደን ልማት ዘላቂ የደን አስተዳደርን ለማንቀሳቀስ ያለመውን የኢትዮጵያን ጊዜያዊ የደን አስተዳደር ደረጃ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም