የለውጡ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የወል ትርክት ለመገንባት እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– የለውጡ መንግሥት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ በውይይት የወል ትርክት ለመገንባት እየሠራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

“ሀገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በክልል ደረጃ የማጠቃለያ በዓል በጎንደር ከተማ ትናንት ተከብሯል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ብዝኃነት ለሀገራዊ መግባባትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መሠረት ነው።

ብዝኃነት የልዩነት ምንጭ እንዲሆን ሲቀነቀን መቆየቱን ገልጸው፥ ይህንን ለመፍታት መወያየት ወቅታዊ አጀንዳ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

ለሰው ልጅ መሠረቱ አብሮነት ነው፤ ሀገርም ይገነባል ለዚህም ደግሞ መግባባት መነጋገርና መረዳዳትን ይጠይቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊነት የሚስተናገዱባት ሀገር ብትሆንም ነጠላ ትርክት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልፀዋል።

የለውጡ መንግሥት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ በውይይት የወል ትርክት ለመገንባት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ብዝኃ ማንነት የሚከበርበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሀገር ያስቀጠለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቅርቡ በክልሉ ፅንፈኝነት የፈጠረው ችግር በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰዋል።

የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን የገለጹት አፈ-ጉባዔው፥ ጫካ የገቡ ልጆቻችንና ወንድሞቻችን በሰላም ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግና ሰላሙን ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ጎን ለጎንም በጎንደር ከተማ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት የሚመጥኑ መሆናቸውን ገልጸው፥ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሥር የሰደደውን ነጠላ ትርክት በውይይት ለመፍታትና የወል ትርክት ለመገንባት ልምምድ ተጀምሯል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን አንድነቷ የተጠበቀ የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት አማራ ክልልም አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You