ዜና ትንታኔ
መንግሥት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክህሎት መር እንዲሆን እየሠራ ነው። ለውጤታማ ኢኮኖሚ ግንባታም ክህሎት ቁልፍ መሠረት መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለመሆኑ ‹‹ክህሎት መር ኢኮኖሚ›› ስንል ምን ማለታችን ነው? እንዴትስ ይገነባል?
አቶ ሙህዲን አባሞጋ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኖሎጂና ሙያ ዘርፍ የሥልጠናና ተቋማት አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዜጎች በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ ባላቸው ክህሎት መጠን ይወሰናል። ሁለም ዜጎች በተለያዩ ሙያዎች ላይ የሚኖራቸው ክህሎት ለጠቅላላው የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ክህሎት መር ኢኮኖሚ ግንባታ ፅንሰ ሃሳብም ይህንን ያቀናጀና የዜጎችን ክህሎት የማዳበር ግብ የያዘ ነው።
‹‹አሁን የምንኖርበት ዓለም ውድድር የበዛበት፣ የሠለጠነ የሰው ሃይል የሚፈልግና ፈጣን የቴክኖሎጂ መለዋወጥ የሚታይበት ነው›› የሚሉት አቶ ሙህዲን፤ ከጊዜው ተለዋዋጭነት ጋር እራስን ማብቃት፣ በክህሎት ብቁ ሆኖ መገኘት የሚጠይቅ ወቅት መሆኑን ያስረዳሉ።
ገበያው ላይ መቆየትና ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው ምርቶችን በብዛትና በጥራት የሚያመርት በተሠማራበት የሙያ መስክ የተካነ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል እንደሆነ ያስረዳሉ።
ኢኮኖሚውን እየመሩ ያሉ ሀገራት የዜጎቻቸው ከህሎት ልማት ላይ በሠሩት መጠን ነው፤ የሚሉት አቶ ሙህዲን፤ ኢትዮጵያም ይህንን መንገድ መከተል እንደሚገባት ያስረዳሉ። ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ፣ ምርቶችን ወደ ውጭ በብዛት መላክ እና የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል አቅም መፍጠር ያስፈልጋል ይላሉ። ይህንን ስኬታማ ለማድረግ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በዜጎች ክህሎት ልማት ሊደገፍ ይገባል ነው ያሉት።
ዜጎች ሙያዊ ብቃታቸው ከፍ እንዲል በኢትዮጵያ መንግሥት ሰፊ ትኩረት መሰጠቱ ተገቢና ወቅቱን ያገናዘበ መሆኑን አቶ ሙህዲን ይናገራሉ። በክህሎትና ምርታማነታቸው ብቁ የሆኑ ዜጎች ለመፍጠር የሪፎርም ትግበራ መጀመሩንም ያስረዳሉ። ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመውጣት የሚያስችል ሉዓላዊነት ለመፍጠር ትግበራዎች መከናወናቸውን ያስረዳሉ።
‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ተግባር ተኮርነት የሚጎለው ነው›› የሚሉት አቶ ሙህዲን፤ ይህም አንድ ዜጋ በሚሠራበት የሙያ መስክ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል (የተፍታታ እጅ) ክህሎት እንዳይኖረው እንቅፋት መሆኑን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ 70 በመቶ ሕዝብ ወጣት መሆኑን የሚያነሱት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ አብዛኛው ወጣት በትምህርትና ሥልጠና ላይ የሚገኝ ቢሆንም በቁጥሩ ልክ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አለመሆኗን ያስረዳሉ። ይህ የሆነው ክህሎትን ያማከለ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ከዚህ ቀደም አለመዘርጋቱ እንደሆነ ያብራራሉ።
የሥልጠና ማእከላት መብዛትና በርካታ ባለሙያዎች መውጣታቸው እሙን ቢሆንም በኢኮኖሚው ውስጥ ግን የሚፈለገውን ተፅእኖ የፈጠሩ አለመሆኑ ይገልፃሉ።
የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው ይህንን ክፍተት በመለየት ክህሎት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ
በመንግሥት መታመኑ ተገቢ ነው የሚሉት አቶ ሙህዲን፤ በተለይ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ክህሎት የማልማት ተግባር ላይ ድርሻቸው ከፍተኛ እንደሆነ ያነሳሉ። ይህንን በሙሉ አቅም መተግበር ሲቻል የሀገር ገፅታ የሚቀይርና ዜጎች በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚያሳድግ መሆኑን ያነሳሉ።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ያህል ክህሎትን ለማልማት ብዙ ይቀራቸዋል የሚሉት አቶ ሙህዲን፤ ወርክሾፖች በሚፈለገው ልክ ተግባር ተኮር ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል አቅም ሊፈጥሩና የዘመኑን ቴክኖሎጂ ሊታጠቁ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ያነጋገራቸው ሌላኛው ባለሙያ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማስፋፊያ አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ አቶ አምላኩ አለባቸው እንደሚሉት ‹‹ክህሎት መር ኢኮኖሚ ተገንብቷል›› ማለት የሚቻለው በተለይ በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት የሚሠጡ ሥልጠናዎች በትክክል በኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችል ተፅእኖ ማሳደር ሲጀምሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹በኢትዮጵያ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማቶች የአካባቢያቸውን ኢኮኖሚ ፀጋ ያማከለ ሥልጠና መስጠት አለባቸው›› የሚሉት አቶ አምላኩ፤ መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በዚህ አግባብ በየአካባቢው ፀጋዎቹን የለየ ምደባዎች እየተከናወነ መሆኑን ያነሳሉ።
በምሳሌነት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚያነሱት አስተያየት ሰጪው አሶሳ ላይ የሚገኙ ማሠልጠኛ ተቋማት ከማእድን ልማት ጋር የተያያዘ የክህሎት ልማት ላይ እንዲያተኩሩ መደረጉን ይገልፃሉ። ይህን መሰል ትግበራ መኖሩ በኢኮኖሚው ላይ በቀጥታ በጎ ተፅእኖ መፍጠር የሚችል የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በባህሪው ከፍተኛ የሆነ ሀብትን የሚጠይቅ መሆኑን የሚያነሱት አቶ አምላኩ፤ ሀብት ውስን በመሆኑ የሚፈለገውን በሙያውና በክህሎቱ ብቁ ሙያ የታጠቀ የሰው ሃይል ለመፍጠር እክል እንደሚፈጠር ይናገራሉ።
ይህንን ችግር ለመፍታት መንግሥት መፍትሄ ማስቀመጡን ተናግረው፤ እያንዳንዱ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ከዘልማዳዊ አሠራር እንዲወጡና በራሳቸው በሥራ ፈጠራ ተሠማርተው ከመንግሥት በጀት የሚላቀቁበት አማራጭ መዘርጋቱን እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቅሳሉ። ይህ መሆኑ ክህሎት መር ኢኮኖሚ ለመገንባትና ዜጎችም በተሠማሩበት ሙያ ላይ አምራችና ብቁ እንዲሆኑ መንገድ እንደሚያበጅ እምነታቸውን ገልፀዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ክህሎት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ይረዳሉ ተብሎ ከታሰቡ መሥሪያ ቤቶች መካከል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ተቋቁሟል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብቁ የሰው ሀብት፣ ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የምትፈጥር ኢትዮጵያን ለመገንባት፣ በተለይ ደግሞ የክህሎት ልማት ላይ ለማተኮር እንደተቋቋመ ማወቅ ይቻላል። የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ሁለቱም የዘርፉ ምሁራን ይህንን መሰል ተቋማት መገንባት እቅዱን ወደ መሬት ለማውረድ እንደሚያግዝ ያምናሉ። ኢንዱስትሪዎች የሚያነሱትን የሠለጠነና ብቁ የሰው ኃይል ችግርን በዘላቂነት እንሚፈታ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም