የሰላም መንገድ አማራጭ የሌለውና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው

አዲስ አበባ፡- የሰላም አማራጭ የሌለው እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መንገድ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ወደ ተዘጋጀላቸው ማዕከላት መግባት መቀጠላቸው ተጠቆመ፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር በሆኑት ጃል ሰኚ ነጋሳ የተመራ የሠራዊቱ  አመራሮች የዓድዋ ድል መታሰቢያን እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንኳን ወደ ሰላም መንገድ መጣችሁ ብለው ተቀብለዋቸዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጃል ሰኚ ነጋሳ የተመሩ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ የሰላም መንገድ አማራጭ የሌለው እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መንገድ መሆኑን በመረዳት መንግሥት ላደረገው ጥሪ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት የሰጡት ምላሽ የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ስምምነቱ የፖለቲካ እና የሃሳብ ልዩነቶችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በውይይትና በሰላም መፍታት ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ በበኩላቸው፤ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው፤ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉት የሕዝብን ጉዳት ለመቀነስ እና የሰላም አማራጭን መቀበል ብልህነትና አዋቂነት መሆኑን በመረዳታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሰላም ስምምነት መፈራረሙን ተከትሎ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት የዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ አንድነት ፓርክን እንዲሁም በአዲስ አበባ የተገነቡ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩልም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ወደ ተዘጋጁላቸው

ማዕከላት መግባታቸውን ቀጥለዋል ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የሠራዊቱ አባላት ወደ ማዕከላቱ በሚያደርጉት ጉዞም ሕዝቡ አቀባበል እያደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል። ሰላም ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ይሁን፣ ይህን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እየገቡ ላሉት ሁሉ ምስጋና ይገባል ብለዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም

Recommended For You