በርካታ የፖለቲካ ጠቢባን የብሪታኒያና አሜሪካ አጋርነትን «የሃያኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ ወዳጅነት» በሚል ይገልጹታል። ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት በፌሽታ ብቻም ሳይሆን ክፉውንም በመጋራት ፀንቶ የቆየው የለንደንና ዋሽንግተን ወዳጅነት፤ በአንዱ ጦርነት ሌላው ለመዝመት እስከ መወሰንም ተሻግሮ ታይቷል።
በእርግጥ እኤአ በ1956 የሜዲትራኒያንና የቀይ ባህርን በሚያቆራኘው ስዊዝ ቦይ ጥበቃ ላይ ብሪታኒያ ከሌሎች አገራት ጋር በፈጠረችው ጥምረት እንዲሁም እኤአ የ1960ዎቹ የአሜሪካና ቬትናም ጦርነት ሁለቱን አገራት ለጊዜውም ቢሆን አኮራርፎ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ሲወሳ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የሚስተዋለው ግን ከኩርፊያም ተሻግሮ በመወራረፍ ሲታጀብ ነው። ይህን ሃሳብ የሚጋራው የሲኤን ኤኑ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ ፒተር በርገን እንደሚገልፀውም፤ በበርካቶች ዘንድ ልዩ በሚል ሲሞገስ የቆየው የሁለቱ ሀገሮች ፍቅር ነፋስ እየገባበት፣ የቀደመው ፖለቲካዊ፤ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውና አጋርነታቸው በእጀጉ እየተቀዛቀዘ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ ግን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነጩን ቤተ መንግስት ከተረከቡ ወዲህ በዋይት ሃውስና ዳውኒንግ ስትሪት መካከል ያለው ሁለንተናዊ አጋርነት እየሻከረ መጥቷል። በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ ነጩን ቤተ መንግስት በተረከቡ ማግስት ወደ ዋሽንግተን በማቅናት የመጀመሪያው የአገር መሪ መሆን የቻሉት ቴሪሳ ሜይ ናቸው።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሯ የነጩ ቤተመንግስት ጉብኝት ግን የአገራቱን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ የነበረው ሚና ከቀናት ዜናነት የተሻገረ አልነበረም። የፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሯ የልዩነት መንገድ አሃዱ ያለውም ብሪታኒያና የአውሮፓ ህብረት በመካከላቸው ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀው የአንድነት ትስስር ገመድ በይፋ ከመበጠሱ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር።
«ከአብሮነት ይልቅ ፍቺ ይሻለኛል»የሚል ጥያቄ ያቀረበችው ብሪታኒያም፤በጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ አማካኝነት የፈለገችውን ለማስፈፀም ላለፉት ዓመታት ያከናወነቻቸው የተለያዩ ተግባራት ደግሞ ለዶናልድ ትራምፕ ማኩረፍ ሁነኛ ምክንያቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሜይ በፍቺው አጀንዳ ላይ የተሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዳልቻሉ በመጠቆም የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ የሚደመጡት ፕሬዚዳንቱ፤ ቆየት ብለው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ምርጥ ተደራዳሪ ናቸው እያሉ ማሞካሸታቸውም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ቅጥ አምባሩ የጠፋበት እየሆነ ስለመምጣቱ ፍንጭ ሰጥቷል።
ብሪታኒያውያንም ቢሆኑ ለቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የሚሰጡት ፍቅር ለትራምፕ የተረፋቸው አይመስልም። ቀደም ሲል አንድ የአሜሪካ መሪ አገራቸውን ሲጎበኝ በሞቀ አቀባባል ሲፈነጥዙ እንደሚስተዋሉት ለትራምፕ ይህን ለማድረግ ፍላጎት የላቸውም።
ዶናልድ ትራምፕ ገና እጩ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ለብሪታኒያ ፓርላማ በቀረበው ከአውሮፓ ህብረት ጋር አብሮ የመቀጠልና የመፋታት ውሳኔ ላይ የመነጠልን ሃሳብ ደግፈው መናገራቸውም በርካታ ብሪታኒያውያን ጥርሳቸውን እንዲነክሱባቸው ዋናኝው ምክንያት ነው።
ፕሬዚዳንቱ ባሳልፈነው ወር ለንደንን ለመጎብኘት ሲወስኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የለንደን ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ያቀረቡት ጠንካራ ተቃውሞና ያስተላለፉት «የአትምጣብን መልእክት» ሁሉም ስለአገራቱ ፍቅር መደፍረስና ህዝቡም ለፕሬዚዳንቱ ስላላቸው ጥላቻ የመናገር አቅሙ የገዘፈ ስለመሆኑ ይታመናል።
ከዘመነ ትራምፕ የፕሬዚዳንትነት ጊዜ አንስቶ የብሪታኒያ ፖለቲከኞች ያውቋት የነበረችው ዋሽንግተን በእጅጉ ተቀይራለች። የብሪታኒያ ዲፕሎማቶችም ከዶናልድ ትራምፕ ጋር መግባባት ተስኗቸዋል። ከቀናት በፊት ይፋ የወጣውና በአሜሪካ የብሪታኒያ አምባሳደር ኪም ዳሮች የትራምፕን አስተዳደር የተቹበት የኢ-ሜይል መልዕክትም ለዚህ ዋነኛ ምስክር ሆኖ ይቀርባል።
አምባሳደሩ አፈትለኮ በወጣው መልዕክታቸው የትራምፕን አስተዳደር «አቅመ ቢስና ክህሎት የሌለው» ሲሉ የተቹ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አምባሳደሩን «እጅግ የማይረባ » ሲሉ ወርፈዋቸዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው አንድ ዓመት በፊት በዋሽንግተን የብሪታኒያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት የ65 ዓመቱ ኪም ዳሮች፥ ከክስተቱ በኋላ፤‹‹በዚህ ሁኔታ ለመቀጠል እቸገራለሁ›› በሚል ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታወቀዋል፡፡
ይህም ክስተት ቀደም ሲል በለንደኑ ከንቲባ ሳዲቅ ካህንና ዶናልድ ትራምፕ እሰጣ አገባ ላይ ተጨምሮበት ወትሮም ቢሆን መልኩ የደበዘዘውን የአሜሪካና ብሪታኒያ ግንኙነት በተለያዩ መሰናክሎች እየተደነቃቀፈ ከባድ ፈተና ላይ ስለመገኘቱ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪሳ ሜይ በምክር ቤቱ ተሰናባቹን ሰው ‹‹እድሜ ዘመናቸውን በብቃት ያገለገሉ ናቸው›› በሚል ማወደሳቸው ደግሞ ‹‹የሁለቱ አገራት ወዳጅነት እየተሸረሸረ ነው›› ለሚሉት በቂ ማስረጃ ሆኖላቸዋል።
አሁን በዲፕሎማሲ ግንኙነት ቀውስ ውስጥ የሚገኙትን ሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደቀድሞው አንድነታቸው ለመመለስ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብለው ለሚጠበቁት ቦሪስ ጆንሰንና ለሌላኛው እጩ ጀርሚ ሃንት ከወዲሁ ከባድ ራስ ምታት መሆኑም ተመላክቷል።
ሁለቱ እጩዎች በአምባሳደሩ ከስልጣን መልቀቅ ላይ የሰጡት መልስና በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም ለየቅል መሆን ደግሞ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል። በዚህ ረገድ የብሎንበርግ አሌክስ ሞራልስና ጆይ ማይስ፤ቀጣዩ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ከታጩት አንዱ የሆኑትና የወቅቱ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት፤«ፕሬዚዳንት ትራምፕ አምባሳደሩን የወረፉበትን መንገድ ስልጣንና ሃላፊነታቸውን የማይመጥን መሆኑን በመጥቀስ ትራምፕ ክብረ ነክ ተግባር ፈፅመዋል ማለታቸውን» አስነብበዋል።
በዋሽንግተን የብሪታኒያን አምባሳር የምት መርጠው አሜሪካ ሳትሆን ብሪታኒያ መሆኗን ለማስገንዘብ አፅእኖት የሰጡት ሃንት፤ እርሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነት የሚቀመጡ ከሆነም ኪም ዳሮች ዳግም በሃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ሰፊ እድል እንዳላቸው የሚነገርላቸው ሌላኛው እጩ ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው፤ አምባሳደሩን ለማግባባትና በሃላፊነት እንዲቆዩ ለማሳመን አሊያም ለተዘነዘረባቸው ወቀሳ ምላሽ ለመስጠት ምንም አይነት አስተያየትና አቋም አለማንፀባረቃቸው ተመላክቷል።
ይህ የቦሪስ ጆንሰን ተግባርም በበርካቶች አልተወደደም። በተለይ የቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆን ሜጀር የጆንሰንን አቋም በመተቸት በአግባቡ ስራቸውን በመስራት የሚታወቁት አምባሳደር በዚህ መልኩ ሃላፊነታቸውን መልቀቃቸው አግባብ አለመሆኑን ለቢቢሲ ራዲዮ ተናግረዋል።
ሌሎች የብሪታኒያ ፖለቲከኞችም ጆንሰን ወዳጃቸው እንደሆኑ ለሚታመኑት ፕሬዚዳንት ትራምፕ መልስ ከመስጠት የተቆጠቡት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን ለመረከብ የሚያደርጉት ጥረት እንዳይከሽፍ በሚል መሆኑን በመጠቆም ተግባሩንም ከራስ ወዳድነት ጋር በእጅጉ አዛምደውታል። «አንድ ለአገር መሪነት የሚጠበቅ ሰው መሰል ክስተቶች ሲፈጠሩ የዜጎችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለ ለቦታው አይመጥንም »የሚሉም በርካቶች ሆነዋል።
ይህ የሰሞኑ ውጥረት በሁለቱ አገራት ላይ በቀጣይ ምን እንደሚከሰት ያተተው የአይሪሽ ታይምስ በበኩሉ፤ ውጤቱ በተለይ «ከብሬግዚት፡ መልስ ብሪታኒያ ከዋሽንግተን ጋር እመሰርተዋለሁ ያለችውን የነፃ ንግድ አጋርነት ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል» ሲል አስነብቧል። አንዳቸው ለአንዳቸው አስፈላጊ የሆኑት ሁለቱ አገራት ፍቅራቸውን አደፍረሰው መጓዝ የሚችሉት በጣም አጭር መንገድ ስለመሆኑ ግን ብዙዎች እርግጠኛ ሆነዋል።
አዲሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ቦሪስ ጆንሰንም የሁለቱን አገራት ግንኙነት በማደስ ረገድ በርካቶች ተስፋ ጥለውባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
ታምራት ተስፋዬ