-ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተሰብስቧል
አዲስ አበባ፡– በክልሉ ከመኸር እርሻ ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ። ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት መሰብሰቡም ተገልጿል።
የክልሉ ምክትል ዕርሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ በመኸር እርሻ ከ345 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአዝርት እህሎች ተሸፍኗል። ከእዚህም ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
በአጠቃላይ በመኸር እርሻ ከተሸፈነው የአዝርት ሰብል ውስጥ ከ118 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ጠቁመው፤ በዘመናዊ እና በባህላዊ የምርት መሰብሰቢያ መንገዶች በመታገዝ የደረሰው ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።
አቶ ማስረሻ እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ በክልሉ የዝናብ ሁኔታው የቀነሰብት ሁኔታ ያለ ቢሆንም፤ ዝናብ በነበረበት ወቅትም የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይከሰት ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል።
በክልሉ የመኸር ጊዜ ረዘም ላለ ወራት እንደሚቆይ የገለጹት ኃላፊው ፤ በመኸር እርሻ ከተሸፈነው ሰብል 45 በመቶ ያህሉ የደረሰ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ ከ 118 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰው ሰብል ነው የተሰበሰበው። ቀጣይ ባሉት ጊዚያት የምርት ማሰባሰብ ሥራው ህብረተሰቡን በማሳተፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አርሶ አደሩ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ መጋዘኖችን በማጽዳት ምርት እንዳይበላሽ በማድረግ ምርቱን ከብክነት የመታደግ ሥራዎችን ሊያጠናክር ይገባል ነው ያሉት።
እንደ አጠቃላይ በክልሉ በመኸር እርሻ በአዝርት እህሎች የተሸፈነው መሬት ከእቅድ አንጻር 95 በመቶ ነው። በአትክልትና ፍራፍሬ አንጻርም የማሳ ሽፋኑ ተመሳሳይ ሲሆን፤ በአንድ አንድ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች በመኸር እርሻ ለማሳካት የተያዘውን እቅድ ተግባራዊ ሆኗል ሲሉ አስረድተዋል።
ሆርቲካልቸርን በተመለከተም 42 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በአትክልትና ፍራፍሬ የተሸፈነ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም ከ15 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ምርት ተሰብስቧል። በዚህም ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።
በመኸር ወቅት በኖራ በታከሙ መሬቶች የአዝርት እህሎችን የመሸፈን ሁኔታ እንደነበር አውስተው፤ በዚህም የተገኘው ውጤት የተሻለ እንደመሆኑ በቀጣይ ትምህርት በመወሰድ ፤ በበልግ ወቅትም መሬትን በኖራ አክሞ የመዝራት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን ያለው እርጥበት ለበልግ እርሻ እና ለበጋ ስንዴ ምቹ እንደመሆኑ፤ የመኸር ሰብሉን በማንሳት ወደ በልግ እና ወደ በጋ ስንዴ ምርት ለመግባት እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም