አዲስ አበባ፡- ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ራስ ገዝ ለመሆን አቅዶ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር )ገለፁ።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የረጅም ጊዜ ልምድ ያለውና ትላልቅ ምሁራንን ያፈራ ከመሆኑ አኳያ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችል አቅም አለው። በአሁኑ ጊዜ ራስ ገዝ መሆን ባይችልም ከሁለት ዓመታት በኋላ ራስ ገዝ ለመሆን አቅዶ ዝግጅት መጀመሩን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በዋናነት የሰነዶች ዝግጅት ላይ እየሠሩ እንዳሉ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን ፕሮግራሞች የሚከለሱበት ሰነድ ተዘጋጅቶ በዚህ ሰነድ መሠረት የዩኒቨርሲቲው ፕሮግራሞች ላይ ክለሳ ለማድረግ ሰነዱ ለሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መቅረቡንና ምላሽ ማግኘቱን ገልፀዋል።
በቀጣይ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት እንዲያየው ፕሮግራም መያዙን ጠቅሰው፤ ሰነዱ ከፀደቀ በኋላ በሰነዱ መነሻነት አጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ያሉ ኮሌጅና ትምህርት ክፍል ፕሮግራሞች ላይ ክለሳ ተደርጎ ራስ ገዝ ለመሆን በሚያመች መልኩ ፕሮግራሞችን እናደራጃለን ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉንም ፕሮግራሞች ይዞ ላይቀጥል ስለሚችል አግባብነት ያላቸውን ፕሮግራሞች ይዞ ለመሄድ ሰነዱ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ፤ እስከ ታህሳስ አጋማሽ 2017 ዓ.ም ለሥራ ዝግጁ እንደሚሆን አስረድተዋል።
የራስ ገዝ ማበልፀጊያ ስትራቴጂያዊ እቅድም እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተው፤ እቅዱ እስከ ታህሳስ መጨረሻ 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ፤ በዕቅዱ ላይም የሚመለከተው አካል ሁሉ አስተያየት ሰጥቶበት፣ ሥራ አመራር ቦርዱ እንዲያውቀው ተደርጎና ተተችቶ ጥር ወር 2017 ዓ.ም በዚህ መነሻነት የምንመራበትን ሰነድ አፅድቀን ሥራ እንጀምራለን ብለዋል።
ከእነዚህ ሥራዎች ባሻገርም አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሕግ ተከልሶ ሙሉ በሙሉ ወደ ማለቁ መድረሱን ጠቁመው፤ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለሴኔት ሥራ አስፈፃሚ ቀርቦ የመጨረሻ ትችት እንደሚቀርብበት ገልፀዋል። ከዚህ በኋላም ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት የሚሸጋገርበትን ጉዞ በተመለከተ በዝርዝር ተተንትኖና ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ እንደሚኖር አስረድተዋል።
እንደ አጠቃላይ በያዝነው 2017 ዓ.ም እነዚህን ሰነዶች የማፀደቅ ሥራ ተሠርቶ በ2018 ዓ.ም ሰነዶቹን ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ እንደሚውሉና 2019 ዓ.ም ላይ ሙሉ በሙሉ ራስ ገዝ ለመሆን በመንግሥት ለማፀደቅና ሥራ ለመጀመር ዝግጁ እንሆናለን የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከሃዋሳ ውጪና ሃዋሳ ከተማ ውስጥ ወደ ሰባት የሚሆኑ የተለያዩ ካምፓሶች እንዳሉት ገልፀው፤ ከስፋቱ አንፃር ውጤታማ አድርጎ በልኩ መምራቱ ላይ ተግዳሮት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በሁለተኛነት ለሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ግንዛቤ ፈጥሮ አብሮ ለመሄድ በስፋት መሥራት እንዳለባቸው ገልፀው፤ ይህም ሌላኛው ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
እነዚህን ዋና ዋና ተግዳሮቶች ለመወጣትም የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ያሳተፈ ሥራ መሥራት አለብን ብለዋል። በተጨማሪም ከአካባቢው መስተዳድር ጋር ተነጋግረውና ራስ ገዝ ለመሆን ያሏቸውን ጉድለቶች መንግሥት አግዞአቸው በተደራጀ ሁኔታ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚመለከታቸውን አካላት ድጋፍ ለመጠየቅ ማሰባቸውንም አስረድተዋል።
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም